ለ አእምሮ / Le'Aimero ለ አእምሮ የጥር 2006 / January 2014/ እትም፣ ቅጽ 2 ቁጥር 6 | Page 50

መቅደሱ ላይ ዱሮ ቄሱ የሚቀድስበትና ሥጋው ወደሙ ሰዎች የሚቀበሉበት ቦታ ወይም ሠርገኞች ቀለበት ተለዋውጠው የፈቃደኛነት ቃለቸውን የሚሰጡበት ሥፍራ ቢራውና ሌሎች መጠጦች የሚቀዱበት „ባንኮኒ“ ነው። በመጽሓፍና በሻማ ፋንታ የአረቄ ጠርሙስና የምግብ ማዘዣ ደብተሮች የሲጋራ መተርኮሻ ትናንሽ ሳህኖች ሹካና ማንኪያ ተቀምጠዋል። አሰላፊ ሠራተኛ ሴቶች ከግራና ከቀኝ ቱር ቱር እያሉ መጠጡንና ምግቡን ዱሮ አግዳሚ ወንበር በነበረበት አሁን ጠረጴዛና ወንበር ይዘው ሲጋራቸውን እያጤሱ ለሚጠብቁ ሰዎች ያቀርባሉ። እምድር ቤቱ ሰለሞላ እኛን ወደላይ ወደ ሠገነቱ ቦታ እንዳለ አንደኛዋ ጠቁማን „ሂዱ ውጡ እኔ እመጣለሁ“ ብላ ሥራዋን ቀጠለች። ምግባችንን አዘን ቢራችንን እና ወይናችንን ጠጥተን ማዕድቤቱ ለመሆኑ የትነው ብዬ ጠየኩ። እሱም ከመቅደሱ ጀርባ እንደሆነ ተነገረኝ። መጸዳጃ ቤቱም -ለወንድና ለሴት ዱሮም ቢሆን የነበረበት ቦታ እዚያው ቤተ-ክርስቲያኑ ምድር ቤት ውስጥ እንዳለ ተነገረኝ። ይህ የዛሬ ሃያ አምስት አመት ታሪክ ነው። አሁን ጊዜው ተቀይሮ የቀድሞ ቤተክርስቲያኖች የወጣቶች ዳንኪራ መራገጫ፣ የልብስና የመጽሓፍት ወይም ሸቀጣሸቀጥ መሸጫ ቤቶች ሁነዋል። አንዳንዴም የሙዚቃ መደገሻ ቤቶችእና የሥዕል ኤግዚቪዥን መድረኮችም ሁነው ያገለግላሉ። አንዳንዶቹ ተሸጠው የግሪክና የራሸያ የሶሪያና የግብጽ ኦርቶዶክሶች ፣ የፖላንድ ካቶሊኮች፣ አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ተከታዮችም ገንዘብ ከአላቸው የሚገዙት ሁነዋል። ይህ ብዙዎቹ ከሆነ አይቀር ሲጠየቁ የሚመኙት ነው። ያለፈው አመት ደግሞ የሓምቡርጉን የእቫንጀሊስት ቤተክርስትያን ለመግዛት እንፈልጋለን ብለው የቀረቡት እንግዶች ሌሎች ሁነዋል። 50