ለ አእምሮ / Le'Aimero ለ አእምሮ የካቲት 2006 / February 2014/ እትም፣ ቅጽ 2 ቁጥር-07 | Page 39

ሌላም መነሳት ያለበት ጉዳይ አለ! በዚያ ኢትዮጵያ በሚባለው ክልልና ግዛት ውስጥ ብቻ መወለዱ በዓለም አቀፍ ሕግ መሰረት አንድን ሰው ወደደው ጠላው ተቀበለው ወይም ይህን አውልቆ ጣለው እሱን ኢትዮጵያዊ ያደርገዋል። ኢትዮጵያዊነት ደግሞ ልክ እንደ አሜሪካኑና እንደ ግብፁ እንደ ሕንዱና ታንዛኒያው ሕዝብን ያስተሳስራል። አንድን ሕዝብ የሚያስተሳስር ሌላው አሁን ወደ መጨረሻው ላይ መጠቀስ ያለበት ተጨማሪ ትልቅ ነጥብ ቢኖር በአዋቂዎች የተነደፈው „ሕገ-መንግሥቱ“ ነው። ሕገ-መንግሥት/ቶች እንደ አገሩ ይለያሉ። የነጻ ሰዎች የግለሰብ መብት የሚያውቀውና የሚያከብረው ዲሞክራቲክ ሕግ መንግሥት ሕዝብን አንድ አድረጎ እንደ ሃይማኖት የሚያስተሳስር ዘመናዊ ምሶሶና ግድግዳ ጣራና አጥር ነው። ፮ ከሁሉም ግን ወይም እላይ ከተጠቀሱት ጉዳዮች ጋር በተጨማሪ አንድን ሕዝብ አንድን አገር -ከሃይማኖትና ከዘር ከመደብና ከሐብት ከዕድሜና ከጾታ ከጉልበትና ከጥንካሬ ከጤና ከደካማ በሽታኛ ከእነዚህ ሁሉ ባሻግር (የሰው ልጆች በሥራቸውም በችሎታቸውም የተለያዩ ናቸው) እነሱን ሁሉ አንድ የሚያደርጋቸው ነገር ቢኖር እርስ በእርስ መተማመንና እሱ ላይ ተመስርቶ የሚገነባው የወንድማማችነት መንፈስና ፍቅር ነው። ይህ በአንድ ሕብረተስብ ውስጥ በጣም ከፍተኛ ቦታ የአለው „የዜጎች ፍቅርና መፋቀር“ ከየት ይመጣል? መተማመን የጠበቀ መተሳሰርንና አንድነትን ወንድማማችንነት በሰው ልጆች መካከል እንዴት ይፈጥራል? 39