ለ አእምሮ / Le'Aimero ለ አእምሮ ሚያዝያ 2006 / April 2014 / እትም፣ ቅጽ 2 ቁጥር 08 | Page 8

ምርምርና አለ ጥናት የኢትዮጵያን ባህልና ኢትዮጵያዊነትን መረዳት አይቻልም። እንዲያውም አውጥተን አውርደን የደረስንበት አንድ ነገር ቢኖር የአገራችን በሽታ ያለው አንድ ቦታ ላይ ነው። እሱም „መንግሥት“ የሚባለው ጽንሰ ሓሳብ ላይ ነው። ከእሱ ለየት የሚለው „አስተዳደር“ የሚባለውም ነገር ላይ ነው። „አገር“ የምባለውም ቃል ትክክለኛ ትርጉም ተፈልጎ በአለመገኘቱና መልስ ስለአልተሰጠውም እንላለን። እነዚህ ሦስቱ (ስቴት ኔሽን ገቨርንመንት) የሰው ልጆችን አሰባስበው በተለያዩ ባህሎችና በተለያዩ ትውፈት በተለያዩ ትሩፋትና እሴቶች …ሥነ -ምግባር እንዲኖሩ ያደረጉ ኮንሰፕቶች (የቻይናው ከሕንድ ይለያል የጀርመኑ ከፈረንሣይ…) በኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ዘንድ „አንድ“ ተደርገው ተጨፍልቀው በመታየታቸው ነው። ይህ ደግሞ ሁሉም ሕዝቡም አገሩም መንግሥትም አስተዳደርም „የኔ ነው“ ወደሚለው የአንድ ቡድን„ጠለፋ ይወስደናል። ዕውነቱን ከተናገርን ከዚያም አልፎ ይሄዳል። …አገርም ብቻ ሳይሆን የአገር ንብረትም መሬቱም ባንኩም ሠራዊቱም ጦሩም የጸጥታ ፓሊሱም ትምህርት ቤቱም ዩኒቨርስቲውም ንግዱም ሕንጻውም መንገዱም እርሻውም „የአንድ ፓርቲ የአንድ ቡድን …“ ተደርጎ ይታያል። ከዚያም አልፎ “አንተ አታስብ እኔ ነኝ ለአንተ የማውቀውም” ወደሚለው ዛቻና ጥላቻም ተሸጋግሮአል። ምን ይደረግ ነገሥታቱም እንደዚህ አድርገው አገሪቱዋን ቀደም ሲል ስለአዩ ወጣቱ ትውልድም “ለእሱ ብቻ” በየፊናው „አደራ ተብሎ የተሰጠው“ ይመስለዋል። ይህ ደግሞ ወደ „…ይገባኛል …ለእኔ ብቻ ይገባኛል“ የሚል ቋንቋና አመለካከት ፍልስፍና የድርጅት መሪዎችንና ተከታዮቹን ወስዶ ኢትዮጵያን እዚህ አሁን ያለችበት ደረጃ ላይ አድርሶአታል። ይህ ብዙ ነገሮችን እንድንረዳ ይጠቅማል። ~8~