ለ አእምሮ / Le'Aimero ለ አእምሮ ሚያዝያ 2006 / April 2014 / እትም፣ ቅጽ 2 ቁጥር 08 | Page 6

ሌላው እላይ የተባለውን እንደገና ለመድገም ከንጉሣዊ ቤተ ሰብ እሰከ ተማሪው ድረስ ባዶ እጁን ነው የወጣው። ለዚህ ደግሞ የስደተኛው ቁጥር ምስክር ነው። የደሃው ብዛት፣ የሚያማርረው ገበሬ፣ ልጆቻቸውን እያስታወሱ የሚያለቅሱ ወላጆች በቂ ማስረጃ ናቸው። ኤርትራ ተገነጠለች ተባለ። ገነትን/ፓራዲይዝን አገኙ? ያ የተባለውንና የተወራለትን በአለፉት ሃምሳ አመታት ….ኦሮሞ ትግሬ አማራ ተባለ። ለመሆኑ„አዲሲቱዋ ኢትዮጵያ ተመስርታ“ አንዲት የምታኮራ መርፌ ብጤ እንኳን አገሪቱዋ ሰርታ የዓለም ገበያ ላይ አወጣች? ትርፉ በሁሉም አቅጣጫ ኪሳራና ቢበዛ ደግሞ አለመደማመጥ ነው። መደማመጥ እንኳን (እንደ አረቦቹ በአለመንጫጫታችን በጨዋነታችን የምንታወቀው) ጠፍቶ (በኢትዮጵያኖች መካከል) በያለበት አሁን መደናቆር ነው። ቀደም ተብሎ የተሰማው እንደ አዲስ ነገር ዛሬ ተነስቶ ይደገማል። ጊዜና ታሪክ መልስ ሰጥቶበት የታለፈው ነገር እንደ አዲስ ተአምር ይነሳል። ሰው የሰለቸው መፈክር እንደ ገና ይወረወራል። በዘመናቸው በጊዜአቸው ቁም ነገር ያልሰሩ ሰዎች ምንም ነገር እንዳልሆነና እንዳልተደረገ „እንደገና እድሉን ስጡን“ ይላሉ። ችግሩ (የኢትዮጵያ) ችግር ያለው ተራው ሰው ጋ አይደለም። ችግሩ ያለው ፊደል የቆጠረው ሰው ጋ ነው። ችግሩ ያለው እነሱ ያስተመሩአቸው የሰበሰቡአቸው ልጆችም ጋ ነው። አገሪቱ ከገባችበት ችግርና ቀውስ የምትወጣው ደግሞ በተያዘው የስህተት ጉዞ ዝም ተብሎ በጭፍኑ ወደፊት ሲራመዱ አይደለም። ~6~