ለ አእምሮ / Le'Aimero ለ አእምሮ ሚያዝያ 2006 / April 2014 / እትም፣ ቅጽ 2 ቁጥር 08 | Page 53

ማህበር ለሁለት መሰነጠቅ የደርግ ደጋፊዎች መሰባሰብ…ወዘተ …ወዘተ… ታሪክ ቀጠለ። እንደገና የዚህ ሁሉጉዞ ድካም ለአገሪቱ ምን አመጣ ተባለ? ቁም ነገሩ እሱ ሳይሆን አንደኛዋ ዝም ብላ የምታዳምጠን ጓደኛችን እንዳለችው „…ቁም ነገሩ ወንድሞቼ ያለው፣ ያለፈው ታሪክ ላይ መነታረክ ሳይሆን ቁም ነገሩ ያለው እኛ የቀረነውና የተረፍነው ሰዎች እንደዚህ ተገናኝተን ስንጫወትና ያለፈውን ዘመን ግንዛቤአችን ውስጥ አስገብተን አንዳንዴ የሚያከራክር ቢሆንም መነጋገር አብረን መቻላችን ነው።….መነጋገር በመካከላችን እሰከ አለ ድረስ ደግሞ ኢትዮጵያ አለች ማለት እንችላለን። ዱሮ ተለያይቶ ተበታትኖ የነበረ ሰው አሁን እኛ እንደምናደርገው በየአለበት መነጋገር ከጀመረ ደግሞ ትልቅ ነገር ነው። ዘመኑ ተቀይሮአል። ይህ ደግሞ ተቀራርቦ መነጋገሩ የአገሪቱ የኢትዮጵያ ተስፋ ነው።እንደዚህ ዓይነቱ ነገር መኖር ደግሞ አዲስ አመለካከትን በሰው ልጆች ዘንድ የሚፈጥረው ነው። በእኔ ግምት“ ቀጥላ እንዳለቺው“ የዕብደት ዘመን በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ትውልድ ያለ ነገር ነው።“ „ልንገራችሁ“ አለች አየር ስባ። „የሓዘን ዘመን አለ። የአእምሮ ቀውስ ዘመን አለ። የኢኮኖሚና የፖለቲካ ክሪዝም ዘመን አለ። ኢትዮጵያን በአለፉት አርባና ሃምሣ አመታት የመታት ቀውስ አውሮፓን አንዴ በሃያኛው ክፍለ -ዘመን ከመታው የአእምሮ ቀውስ ጋር የሚነጻጻር ነው። ከማድሪድ እሰከ ሞስኮ ከባልካን አስከ ፓሌርሞና ኦስሎ የተለያዩ አይዲኦሎጂዎች ተነስተው ይህቺን አህጉር አተራምሰዋታል።“ „ታዲያ አሁን እኛ ከገባንበት ቀውስ ልንወጣ እንችላለን ነው የምትይው?“ አላት አንዱ። ~ 53 ~