Christian Books & Magazines - Free Berea Magazine 5 | Page 8

ከብልጡጎች ጋር አይደለም ። እንዲህ ሲባል ኢየሱስ የብልጡጎች ጠላት ነው ማለት አይደለም ። ኢየሱስ ድሆች ተመልካችና ተሟጋች እንደሌላቸው ያውቃል ። በመሆኑም እርሱ ከጎናቸው ካልቆመ ማንም አይቆምላቸውም ። ኢየሱስ ባለጠጋ ነኝ የሚሉ ሰዎችን ሁልጊዜ የሚላቸው ያላችሁን ሽጣችሁ ለድሆች ስጡ ነው ። ለብዙ ባለጠጎች እንዲህ ዐይነቱ ትእዛዝ የሚዘገንንና የሚጎመዝዝ ነበር ። ለኢየሱስ ከምንም በላይ የሚበልጠው በእግዚአብሔር ዘንድ ሀብታም ሆኖ መገኘት ነው ( ሉቃ 12 ፥ 21 )። በእግዚአብሔር ዘንድ ሀብታም መሆን ማለት ምድራዊውን ሕይወትና መመዘኛ ንቆ በሰማያዊው ሐሳብ መወረስ ማለት ነው ። ምድራዊ ብልጽግና በሰዎች ፊት እንደ ትልቅ ነገር ይቈጠር ይሆናል ፤ በእግዚአብሔር ፊት ግን ፋይዳ ቢስ ነው ፤ “ በሰዎች ዘንድ የከበረ ፣ በእግዚአብሔር ፊት የረከሰ ነውና ” ( ሉቃ 16 ፥ 15 )። ምናልባት ለምንድን ነው ብልጥግና የተጣጣለው ? ማለትም ምንም ረብ እንደሌለው ነገር የተቈጠረው ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል ። ብልጽግና ለፈተና ይዳርጋል ፤ ልብ ያሳብጣል ፤ ወይም በራሱ በመጽሐፍ ቅዱስ ቋንቋ “ ጥጋበኛ ” ያደርጋል ( ዶናልድ ትራምፕን ልብ ይሏል )። መጽሐፍ ቅዱስ ብልጽግና እግዚአብሔርን ወደ መርሳትና ወደ መተው ከዚያም በራስ ወደ መታመን ያደርሳል በማለት ያስጠነቅቃል ። ከባርነት ቤት ነጻ የወጣችውና በእግዚአብሔር የበለጸገችው እስራኤል ታዳጊ አምላኳን የረሳችበት ጊዜ ነበር ፤ “ ከተሰማሩ በኋላ ጠገቡ ፤
በጠገቡም ጊዜ ልባቸው ታበየ ፤ ስለዚህ ረሱኝ ” ( ሆሴ 13 ፥ 6 )። በሕጉ መሠረት በእስራኤል የሚነሡ ነገሥታት ብርና ወርቅ ለራሳቸው ማከማቸት የለባቸውም ( ዘዳ 17 ፥ 16-17 )። ለንጉሥ ሰሎሞን ፣ ለኢዮሳፍጥና ለሕዝቅያስ መውደቅ ምክንያቱ ሀብት ነው ( 1ነገ 3 ፥ 11-13 ፤ 10 ፥ 23 ፤ 1ዜና 29 ፥ 28 ፤ 2ዜና 1 ፥ 11- 12 ፤ 9 ፥ 22 ፤ 2ዜና 17 ፥ 5 ፤ 18 ፥ 1 ፤ 2ዜና 32 ፥ 27 )።
መጽሐፍ ቅዱስ ምድራዊውን ብልጽግና ሳይሆን ሰማያዊውን ብልጽግና እንድንሻ ያሳስበናል ። ነገር ግን እንዴት መበልጸግ እንደምንችል አያስተምርም ፤ ስለ ብልጽግና መንገድም ሆነ ስልት ምክር አይሰጥም ። ብልጽግናን እንደ ትልቅ መንፈሳዊ ትምህርት ቈጥረው የሚሰብኩ ሰዎች እንደ አሸን ቢፈሉም በእውነተኛው ከቊጥር የሚገባ ትምህርት አይደለም ። የብልጽግና ወንጌል የሰዎችን ሁሉ ችግር አይፈታም ። የብልጽግና ወንጌል ባለጠጎች ዘንድ ሲደርስ ይሽመደመዳል ፤ ምክንያቱም ምኑን ያበለጽጋቸዋል ፤ እነርሱ ራሳቸው ገና ድሮ ባለጠጎች ናቸው ። የብልጽግና ወንጌል ባለጠጎችን አያጓጓም ። የብልጽግና ወንጌል የሚያጓጓው ምስኪን ድሆችን ብቻ ነው ። ምናልባትም ብዙ የሚሰበከውና ብዙ የሚዘከረው በድሆች ሰፈር ነው ። እብልጡጎች ሰፈር ብልጽግና አይሰበክም ። 5 የብልጽግና ወንጌል ሁልጊዜ የሚያጓጓውና የሚያሳሳው “ በምድራዊው ሕይወትና መመዘኛ ” ያልተሳካላቸውን ሰዎች ነው ። በምድራዊው ሕይወትና መመዘኛ ተሳካላቸው የሚባሉት የሆሊውድ
ስታሮችና ቢል ጌትስ ከሆኑ በብዙ ሚሊዮን የምንቈጠር ሰዎች ከስረናል ማለት ነው ። የስኬት መለኪያው ሀብት ፣ ስምና ዝና አይደለም ፤ መጽሐፍ ቅዱስ ብልጽግናን እንደ ስኬት ጨርሶ ቈጥሮት አያውቅም ። እንዲህ ዐይነቱ ትምህርት ብዙ የሚሰበከውና ብዙ የሚዘከረው በዚህ ዓለም መመዘኛ ራሳቸውን ሰፍረው በቀለሉ ሰዎች መንደር ነው ። በመሠረቱ የሰዎች ትልቁ ችግር ማግኘትና ማጣት አይደለም ፤ ወይም ሀብትና ድህነት አይደለም ። የሰዎች ትልቁ ችግር ኀጢአትና መዘዙ ነው ። በዚህ ረገድ ሰዎች ሁሉ – ሀብታምም ሆኑ ድሀ – እኩል ናቸው ። ሀብታሞችም ሆኑ ድሆች ኀጢአተኞች ናቸው ፤ እናም ለድሆች ኢየሱስ እንደሚያስፈልግ ሁሉ ለሀብታሞችም ኢየሱስ ያስፈልጋቸዋል ።
ሰዎች ሁሉ ኀጢአተኞች ከሆኑ ኢየሱስ የማያስፈልገው ምድራዊ የለም ። ጳውሎስ “ ሰዎች ሁሉ ከኀጢአት በታች ” መሆናቸውን ሲናገር “ ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ ፤ አስተዋይም የለም ፤ እግዚአብሔርንም የሚፈልግ የለም ፤ ሁሉም ተሳስተዋል ፤ በአንድነትም የማይጠቅሙ ሆነዋል ” ይላል ( ሮሜ 3 ፥ 9-11 )። ጳውሎስ ችግራችን ምን እንደ ሆነ ከነገረን በኋላ መፍትሔውንም ነግሮናል ። “ አሁን ግን በሕግና በነቢያት የተመሰከረለት የእግዚአብሔር ጽድቅ ያለ ሕግ ተገልጧል ፤ እርሱም ለሚያምኑ ሁሉ የሆነ በኢየሱስ ከርስቶስ በማመን የሚገኘው ጽድቅ ነው ” ( ሮሜ 3 ፥ 21-22 )። ምንም ተባለ ምን ክርስቲያኖች ከክርስቶስ የተነሣ ገና ድሮ ባለጠጋ ናቸው ፤ ምንም እንኳ ዐውዱ
8