Christian Books & Magazines - Free Berea Magazine 5 | Page 7

በኢኮኖሚያዊ ሀብቷ ላይ ነው ። የሮም ዝና መላውን ምድር እንዴት ማጥለቅለቅ ቻለ ? ተብሎ ቢጠየቅ መልሱ ከብዝበዛ አያልፍም ። በምዕራፍ 13 ላይ የሮም ወታደራዊ ኀይል ሲወደስ (“ አውሬውን ማን ይመስለዋል ? እርሱንስ ማን ሊዋጋ ይችላል ?” 13 ፥ 4 ) በምዕራፍ 17 ላይ የሮም ኢኮኖሚያዊ ሀብት ተወድሷል (“ ታላቂቱን ከተማ የምትመስላት ምን ከተማ ነበረች ” 18 ፥ 18 )። ላይ ላዩን
ከተመለከትነው እነዚህ አገላለጾች ተራ ውዳሴ ሊመስሉን ይችላሉ ። ይሁንና ሮም ራሷን ከእግዚአብሔር ሥልጣንና ክብር ጋር እንዳስተካከለች ያሳያል ። ሮም በኀይልና በሀብት መግነኗ አንሶ ራሷን አመለኮተች ፤ “ ንግሥት ሆኜ እቀመጣለሁ ፤ ባልቴትም አልሆንም ፤ ኀዘንም ከቶ አላይም ” ( 18 ፥ 7 ) ። እዚህ ላይ ማተኮር የምፈልገው በሮም ብልጽግና
ላይ ይሆናል ። በራእዩ ውስጥ በግልጽ እንደተመለከተው የሮም ብልጽግና የተመሠረተው በግፍ ብዝበዛ ላይ ነው ። ሮም ጉልበት አለኝ ብላ አገሮችን ሁሉ በዝብዛለች ። ከብዝበዛ ባገኘችው ሀብት ግን ራሷን ከማቀማጠል ያለፈ ነገር አላደረገችም ። ዮሐንስ “ ሴቲቱም በቀይና በሐምራዊ ልብስ ተጐናጽፋ በወርቅና በከበሩ ድንጋዮች በዕንቈችም ተሸልማ ነበር ” ( 17 ፥ 4 ) ሲለን የባለጠግነቷን ልክ እየነገረን ነበር ( 18 ፥ 15-17 )። ለሮም ቅምጥልነት ሲባል ከየአገሩ የከበሩ ድንጋዮች ሁሉ ተዘርፈው መጥተዋል ( 18 ፥ 12-13 )። የሰዎች ነፍስ እንኳ ሳይቀር ለሮም ቅምጥልነት ተገብሯል ( 18 ፥ 13 )። ሮም “ የሮሙ ሰላም ” ( Pax Romana ) በሚለው መፈክሯ የዓለምን ነገሥታት ብታነኾልልም ከሰጠችው ይልቅ የዘረፈችው ይበልጣል ። እግዚአብሔር በሮም ላይ የሚፈርደው ሌሎችን በዝብዛና አደህይታ ራሷን ስላከበረችና ስላቀማጠለች ነው ( 18 ፥ 7 )። ዮሐንስ የሮምን ግፍ ለመግለጽ ወደ 28 የሚደርሱ “ ጭነቶችን ” ዘርዝሯል ( 18 ፥ 12-13 )። ጭነቶቹ በግፍ ተዘርፈው የመጡት ከሦስት አህጉራት ሲሆን ፤ ከአውሮፓ እስፔን ፣ ግሪክ ፤ ከአፍሪካ ሞሮኮ ፣ ግብጽ ፣ ሶማሊያ ፤ ከእስያ ደግሞ ከሶሪያ ፣ ከየመን ፣ ከቻይና ፣ ከሕንድ ፣ ከኢንዶኔዥያ ነው ። እነዚህ ጭነቶች አብዛኞቹ ቅምጥልነትን የሚያንጸባርቁ
ናቸው ( 18 ፥ 14 )። 4 ሌሎችን በዝብዛና አደህይታ በብልጽግና ዙፋን ላይ የተቀመጠችው ሮም ብርቱ ፍርድ እንደሚጠብቃት ተነግሯታል ። ሮም የሚፈረድባት የእግዚአብሔርን ፍጥረት ስላጐሳቈለች ነው ። በእግዚአብሔር ፍጥረት ራሱ ፈጣሪው እግዚአብሔር መክበር ሲገባው ሮም ክብሩን ለራሷ ወሰደች ። ሁሉም ግን ጊዜአዊ ነበር ( 18 ፥ 21-24 )።
በብሉይ ኪዳን ብልጽግና መልካም እንደ ሆነ ቢነገርም ባለጠጎች ግን ሁልጊዜ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል ፤ ማለትም ብልጽግና ባይኮነንም ባለጠጎች ግን ተኮንነዋል ። ሀብት ራሱ ሳይሆን ባለጠጎች ከፍርድ በታች እንደ ሆኑ ተነግሯቸዋል ። በአንጻሩም በአዲስ ኪዳን ብልጽግና ሲወደስ አናነብም ። “ እንዲያውም በአዲስ ኪዳን ውስጥ የብልጽግናን መልካምነት የሚያወሳ አንድም ጥቅስ የለም ። በመሠረቱ በመላው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ገንዘብ የቀረበ ጸሎት ከቶውን የለም ።” ምናልባት አንዲት ጥቅስ አለች ፤ እርሷም ብትሆን በቀጥታ የቀረበች ጸሎት አይደለችም (“ ድህነትንና ባለጠግነትን አትስጠኝ ”፤ ምሳ 30 ፥ 8 )። ገንዘብም ሆነ ብልጽግና ከኢየሱስ አንጻር ተኮንኖ ተብጠልጥሏል ። ኢየሱስ ሁልጊዜ ራሱን የደመረው ከድሆች እንጂ
4 ከዚህ ጋር የሚመሳሰል አንድ ታሪክ መጥቀስ ይቻላል ። በአሁኑ ጊዜ የዝሆን ጥርስ ዋጋው ከወርቅ ዋጋ ጋር እየተስተካከለ መጥቷል ። የዚህ ምክንያቱ የቻይና ሀብታሞች ናቸው ፤ የቻይና ሀብታሞች የብልጥግናቸውን ልክ ለማሳየት የሚጥሩት ቤታቸውን ለማስጌጥ በሚገዙት የዝሆን ጥርስ ነው ፤ ለሩቅ ምሥራቃውያን በተለይም ለቻይኖች የዝሆን ጥርስ የሀብትና የብልጥግና መግለጫ ነው ። በጣም የሚያሳዝነው በአፍሪካ የዝሆኖች ቊጥር እየተመናመነ ሲመጣ በቻይና የሀብታሞች ቊጥር እየጨመረና ፍላጎታቸውም እየበረከተ መምጣቱ ነው ። ለቻይኖች ፍላጎት ሲባል የአፍሪካ ዝሆኖች ከምድረ ገጽ መጥፋት አለባቸው ። እንዴት ያለው ጭፍንነት ነው አቦ !!
“ ሀብታም ነኝና ባለጠጋ ሆኜአለሁ ፤ አንድም ስንኳ አያስፈልገኝም የምትል ስለሆንህ ጐስቋላና ምስኪን ድሀም ዕውርም የተራቈትህም መሆንህን ስለማታውቅ ባለጠጋ እንድትሆን . . . ዐይኖችህን የምትኳለውን ኲል ከእኔ እንድትገዛ እመክርሃለሁ ” ( ዮሀ ራዕይ 3 ፥ 17-18 )።
7