Christian Books & Magazines - Free Berea Magazine 5 | Page 46

ኢየሱስ እኛን ለማዳን የሞተውና ሞትን ድል አድርጎ
የተነሣው ባለፉት ዓመታት ስለሆነ ( ሮሜ 10 ÷ 9 ፣ 1ቆሮ 15 ÷ 1-11 )። እምነት የመጪውንም ጊዜ እውነት ማዕከል ያደረገ ነው ። ይኸውም በሕይወት ዘመናችን እውን ያልሆኑ ነገሮች ፣ ነገር ግን እግዚአብሔር ይፈጽምልናል የምንላቸው ቃል ኪዳኖች ( ተስፋዎች ) ሁሉ መጪውን ጊዜ የሚያመለክቱ ናቸው ( ዕብ 11 ÷ 6 )። ከብሉይ ኪዳን ቅዱሳንም የምንማረው ይህን ባሕርይ ነው ( ሮሜ 6 ÷ 8 ፤ 2ጢሞ 1 ÷ 12 )። ይህ የሚያሳየን እምነት መጪውንም ጊዜ የሚያመለክት እንደ ሆነ ነው ( 1ተሰ 4 ÷ 14 )።
እምነት እግዚአብሔር የሰጠንን ተስፋ እውን ያደርገዋል ( ይፈጽመዋል ) ብለን የምንታመንበት መሠረት እንጂ ፣ አንድ ነገር የእኛ እንዲሆን የምናስገድድበት ( የምናዝበት ) መሣሪያ አይደለም ። እምነት እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን መግቦት ( Providence ) ዛሬም ሆነ ወደ ፊት የምናረጋግጥበት ምልዕቅ ነው ።

የአዎንታዊ አዋጅ ግምገማ

የእንቅስቃሴው መምህራን ፣ አዎንታዊ ዐዋጅን አስመልክቶ አበክረው ከሚጠቅሷቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምንባባት መኻል ሮሜ 10 ÷ 10 ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዝ ይመስለኛል ፣ “ ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና ፤ በአፉም መስክሮ ይድናልና ”። የእንቅስቃሴው መሪዎች ከዚህ ጥቅስ በመነሣት የተፈለገን ነገር ማግኘት የሚቻልበትን “ ቀመር ” ቀምረዋል ፤ “ ሕግ ” ደንግገዋል ። ነገር ግን የክፍሉ ዐውድ ይህን በጭራሽ የሚደግፍ አይደለም ። በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ፣ የሮማውያን ቄሳሮች አምላክ ነን የሚል አቋም ነበራቸው ። ግዛተ ዐፄአቸውንም አምላከ ገዝ ( ቴዎክራቲክ ) ብለው ይጠሩ ነበር ። ቄሳር ጌታ ነው ማለትም የሮማዊነት ዐይነተኛ ምልክት ነበር ። ክርስቲያኖች ግን ቄሳር በፍጹም ጌታ አይደለም ፤ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው በሚለው አቋማቸው ጸኑ ።
በዚህ ምክንያት ለአናብስት ይሰጡ እንደ ነበር ፣ በግንድ ላይ ታስረው በእሳት ይቃጠሉ እንደ ነበር ታሪክ ያስተምረናል ። በዚያን ዘመን ኢየሱስ ጌታ ነው ብሎ በአፍ መመስከር ፣ የሕይወት ዋጋ የሚያስከፍል ትልቅ ወንጀል ነበር ። መጽሐፍ ቅዱስ ፣ “ ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር … ትድናለህ ” ብሎ ሲናገር ፣ ይህን ታሳቢ ባደረገ መልክ ነው ። ስለዚህ ሰው የኢየሱስን ጌትነት በልቡ
አምኖ ፣ “ ቄሳር ጌታ ነው ” ብሎ በአፉ ሊመሰክር አይችልም ። ምክንያቱም አምላካችን እግዚአብሔር ፣ “ ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይኑሩህ ” ብሏልና ።
ዕብራውያን ደግሞ የብሉይ ኪዳንን ሕግ በመፈጸም ጽድቅ እንደሚገኝ ያምናሉ ፤ በአፋቸውም ይመሰክራሉ ፤ ነገር ግን ዕብራውያኑ ይህን በማድረጋቸው ትክክል አይደሉም ( ሮሜ 9 ÷ 30 ፤ 10 ÷ 3 )። ማመንና መመስከር ብቻውን ለውጥ አያመጣም ። ከዐውዱ እንደምንመለከተው ጳውሎስ እመኑ ፤ በአፋችሁም መስክሩ የሚለው ፣ “ ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ ፤ እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው ” ነው ። ይህን ታሪካዊ ንግግር በማዛባት የሰዎች ንግግር አዎነታዊም ሆነ አሉታዊ ውጤት አለው የሚለው የእንቅስቃሴው ትምህርት በዚህ ጥቅስ ላይ መደገፍ በፍጹም አይችልም ። ሌላው ፣ “ ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ ፤ እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው ” እኛ ብናምን ወይም ባናምን ፤ በአፋችን ብንመሰክር ወይም ባንመሰክር ፣ እውነታውን እውነት ከመሆን የሚቀንሰው ( የሚከለክለው ) አንዳችም ምክንያት የለም ። ስለዚህ ኬኔት ሐጌንም ሆኑ ቢጤዎቻቸው ፣ “ አንድ ሰው ድኛለሁ ብሎ ካላወጀ በስተቀር ፣ ድነት አያገኝም ” 28 እንዲሁም ሰው የተናገረውን ማናቸውንም ነገሮች ያገኛል የሚለው ትምህርታቸው ፣ በቃለ እግዚአብሔር የተደገፈ አይደለም ።
ከላይ እንደ ተመለከትነው ፣ የምናገኛቸው ክፉም ሆኑ መልካም ነገሮች ሁሉ ፣ በእምነት ተሞልተን በቃላት በምንገልጸው ነገር ይወሰናሉ ” ለሚለው ትምህርት የእንቅስቃሴው መምህራን የሚጠቅሱት ሌላው ጥቅስ ማቴዎስ 9 ÷ 29 ፣ “ እንደ እምነታችሁ ይሁንላችሁ ብሎ ዐይኖቻቸውን ዳሰሰ ” የሚለውን ነው ። ነገር ግን ኢየሱስ እነዚህ ሰዎች ወደ እርሱ ሲመጡ ፣ ፈውስ ገንዘባቸው እንደ ሆነ እንዲያምኑ ፣ ተፈውሻለሁ ብለው እንዲያውጁ ” ሲያበረታታቸው ወይም “ እኔ የምፈውሳችሁ እምነት ሲኖራችሁ ብቻ ነው ” ሲላቸው አንመለከትም ። ይልቁንም ፣ ይህን ማድረግ እንድችል ታምናላችሁን ?” ( ቊ 28 ) ብሎ ሲጠይቃቸው እንጂ ፤ ይህ የሚያሳየን ዐይነ ስውሮቹ ፣ የተፈወሱት በእምነታቸው ሳይሆን ፣ በኢየሱስ ፈዋሽነትና ደግነት ነው ። ኢየሱስ ሊፈውሳቸው እንደሚችል ማመናቸውን ተጠየቁ እንጂ ፣ “ ፈውስ የእኛ ነው ” ብለው እንዲያውጁ አልተጠየቁም ። ፈውስን ከኢየሱስ ለመቀበል እምነት አስፈላጊ ነው ፤ ነገር ግን ለፈውስ ብቸኛው ምክንያት አይደለም ።
46