Christian Books & Magazines - Free Berea Magazine 5 | Page 45

ራሱ እግዚአብሔር ብቻ ነው ። አብርሃም በእግዚአብሔር ያመነበት ዐይነተኛው ምክንያት ፣ “ ለሙታን ሕይወት ስለሚሰጥ ፤ ያልነበረውንም እንደ ነበር ስለሚያደርግ ነው ” ( ቊ 17 )። የተስፋውን ቃል የሰጠው እንዲሁም የተስፋውን ቃል የፈጸመው ራሱ እግዚአብሔር ነው ( 4 ÷ 20-21 )።
“ ክርስቲያን ጤንነትንና ብልጽግናን የራሱ እንደ ሆኑ በማመን ፣ ያመነውንም ነገር እውን ይሆንለት ዘንድ በማወጅ ፣ ያሻውን ነገር ያገኛል ” ለሚለው የእንቅስቃሴው ትምህርት የሚጠቀሰው ጥቅስ ኤፌሶን 1 ÷ 3 ነው ። ነገር ግን ሐዋርያው ጳውሎስ በክፍሉ ላይ የሚዘረዝራቸው በረከቶች ሁሉ ቁሳዊ ሳይሆኑ መንፈሳውያን ናቸው :—
1 . የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችን ( ቊ 5 ) 2 . በደሙ የተደረገውን ቤዛነታችንንና የኀጢአት ስርየት ማግኘታችን ( ቊ 7 )
3 . የፈቃዱን ምስጢር ማወቃችን ( ቊ 9 ) 4 . የእግዚአብሔር ርስት ወራሽ መሆናችን ( ቊ 11 ) 5 . በመንፈስ ቅዱስ መታተማችን ( ቊ 13 )
በዐውዱ ውስጥ የምናገኛቸው እነዚህ በረከቶች ሁሉ መንፈሳውያን እንጂ ፣ ስለአካላዊ ጤንነት ወይም በንዋይ / በገንዘብ በኲል ስለሆነው ብልጥግና የሚናገሩ አይደሉም ። መንፈሳዊው ነገር በእምነት ቁሳዊ መሆን እንደሚችል የሚናገሩ አይደሉም ።
እምነት በጭራሽ ቁሳዊ የሆነውን እውነታ የሚክድ አይደለም ። ለምሳሌ የአብርሃምን ታሪክ ከሮሜ ምዕራፍ 4 እንመልከት ። በክፍሉ አብርሃም የአካሉን ማርጀት እንዲሁም ልጅ ለመውለድ ዐቅም እንደ ሌለው ሲክድ አንመለከትም ። ምውት የሆነውን የእርሱንና የባለቤቱን አካል ፣ ራሱ እግዚአብሔር በኪነ ጥበቡ ሕያው በማድረግ ልጅ እንደሚሰጣቸው አመነ እንጂ ። ይህ የእምነት ሰው ፣ ሙት የሆነውን የእርሱንና የባለቤቱን አካል እየካደ ሲናገር አንመለከትም ( ቊ 19 )። እንቅስቃሴው ግን እምነት እውነታን መካድ ነው እንዳለ ልብ ይሏል ።
የእንቅስቃሴው መምህራን ፣ “ የሚታየውን እንጂ የማይታየውን ባንመለከት ”( 2ቆሮ 4 ÷ 18 ) የሚለውንም ጥቅስ አዘወትረው ይጠቅሳሉ ። ነገር ግን በክፍሉ ሐዋርያው ጳውሎስ እያለ ያለው ፣ ቁሳዊ እውነታዎችን እንካድ ሳይሆን ፣ የሕይወታችን መሠረት ሊሆን የሚገባው የሚታየውን ጊዜያዊ የሆነው ነገር ሳይሆን ፣ ዘላለማዊና ከሚታየው ነገር በላይ የሆነው ነገር መሆን ይገባዋል የሚል ትምህርት ነው ። እንዲያውም
ሐዋርያው በዚሁ ዐውድ ፣ “ የውጭው ሰውነታችን ቢጠፋ ” የሚለው ሐረግ የሚያሳየን ፣ አካላችን እንደሚሞትና እንደሚበሰብስ የሚያስረግጥ ነው ። የእንቅስቃሴው መምህራን ግን ይህ ዐይነቱን የጳውሎስ ንግግር ፣ “ አሉታዊ ዐዋጅ ” በማለት ያጣጥሉታል ። ሐዋርያው ጳውሎስ ግን ቁሳዊ እውነታን መናገር ነውር ነው ወይም እውነታን መካድ እምነት ነው የሚል ትምህርት አያስተምርም ።
“ በእምነት እንጂ በማየት አንመላለስምና ” ( 2ቆሮ 5 ÷ 7 ) የሚለው የጳውሎስ ንግግር ፣ “ ማየትን ” ወይም የገሐዱን ዓለም እውነታ የሚቃወም አይደለም ። ነገር ግን ሕይወት የሚመዘነው አሁን እየኖርንበት ባለው ሕይወት ስላልሆነ ፣ በእግዚአብሔር ዘላላማዊ ተስፋ ካመን ፣ ያለመሞትና በትንሣኤ ጊዜ የከበረ ሕይወት ባለቤቶች እንሆናለን ለማለት ነው ( ቊ 1-8 )። ልብ ልንለው የሚገባን ሌላው ነጥብ ፣ እምነት ምክንያታዊነትን ( አ መ ክ ን ዮ ን ) ይቃወማል የሚለው አስተሳሰብ ስሕተት ነው ።
እምነት በፍጹም ኢምክንያታዊነት አይደለም ። እንደ መጽሐፍ ቅዱሳዊው ትንተና ፣ እምነት ዓለማትን የፈጠረውና ዓለማትን በእውነት በሚያስተዳድረው ልዑል አምላክ መተማመን ስለሆነ ። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱሳዊው እምነት የዕውቀትና የመረዳት መጠናችንን ውሱንነት ያገናዘበ ነው ። “ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ ” ( ምሳሌ 3 ÷ 5 ) ማለት ፣ ኢምክንያታዊ ሁን ማለት ሳይሆን ፣ ሕይወትህን ለመምራት በራስህ ብቃት ስለሌለህ በእግዚአብሔር ዕውቀትና እርሱን በማክበር ኑር ማለት ነው ( ቊ 6-7 )።
እምነት የአሁን ጊዜ ( Present tense ) ጒዳይ ነው ፣ የሚለው የእንቅስቃሴው ትምህርት መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም ። በእንግሊዝኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጒሞች ላይ ፣ የአሁን ጊዜ የሚያመለክቱ ግሦችና ( is ) ቃላት ( now ) ጥቅም ላይ የዋሉት ፣ ለሐሳብ ፍሰትና የዐረፍተ ነገሩን ሽግግር ለማሳለጥ እንጂ ፣ የጊዜን ቅደም ተከተል እንዲያመለክቱ ታስቦ አይደለም ፤ ለምሳሌ :— 1ቆሮ 7 ÷ 1 ይመለከቷል ። የአሁን ጊዜን የሚያመለክተው ረዳት ግሥ ( is ) የእምነት ትንታኔ ለመግለጽ የገባ እንጂ ፣ ጊዜን ለማመልከት አይደለም ።
እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ፣ እምነት የዐላፊ ፣ የአሁን እንዲሁም የመጪውን ጊዜ እውነታ አቀናጅቶ የያዘ ነው ። እምነት የአሁን ጊዜ እውነታ ስለሆነ ፣ በእግዚአብሔር ላይ ያለንን እምነት የሚያሳይ ነው ፤ ይኸውም እግዚአብሔር እንደሚወደን ፣ ከእኛ ጋር እንደሚኖር ወዘተ ( ሮሜ 5 ÷ 13 )። እውነት የዐላፊ ጊዜ እውነታንም ማዕከል ያደረገ ነው ።
45