Christian Books & Magazines - Free Berea Magazine 5 | Page 4

በዚህ አጭር መጣጥፍ መጽሐፍ ቅዱስ ብልጽግናን በተመለከተ የሚያስተምረው ምንድን ነው ? የሚለውን ለመመልከት ጥረት እናደርጋለን ። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ብልጽግና የሚያስተምረውን ከመመልከታችን በፊት “ የብልጽግና ወንጌል ” ምን እንደሚያስተምር በጥቅሉ መዳሰስ ይኖርብናል ። የብልጽግና ወንጌል አስተምህሮ በአብዛኛው የተመሠረተው በመዝ 34 ፥ 10 ፤ 37 ፥ 25 እና በ3ዮሐ 2 ላይ ነው ፤ መዝሙረኛው “ እግዚአብሔርን የሚፈልጉ ግን ከመልካም ነገር ሁሉ አይጐድሉም ”፤ “ ጻድቅ ሲጣል ዘሩም እህል ሲለምን አላየሁም ” ይላል ። ዮሐንስ በበኩሉ “ ወዳጅ ሆይ ፤ ነፍስህ እንደሚከናወን በነገር ሁሉ እንዲከናወንልህና [ እንድትበለጽግና ] ጤና እንዲኖርህ እጸልያለሁ ” ይላል ። ትምህርቱን ባጭሩ “ ብልጽግና የእግዚአብሔር በረከት ነው ፤ ድህነት የእግዚአብሔር እርግማን ነው ” በሚለው ማጠቃለል ይቻላል ። ብልጽግና የበረከት እንዲሁም ድህነት የእርግማን ምልክት ከሆነ ለመባረክና ከድህነት ለመውጣት ምን እናድርግ ? የትምህርቱ መሐንዲሶች በርካታ መፍትሔ አላቸው ፤ መፍትሔዎቹ በሁለት ፈርጅ መመደብ ይችላሉ ። አንደኛው መፍትሔ “ አዎንታዊ አዋጅ ” ( positive confession ) ነው ። እባረካለሁ ብለህ አውጅ ፤ እበለጽጋለሁ ብለህ አውጅ ፤

4

መጽሐፍ ቅዱስና ብልጽግና ከወንድም ምኒልክ አስፋው

የችግሬ ሥር ከነ ሰንኮፉ ተነቅሎ ጦሴን ይዞ ከእኔ ይወገዳል ብለህ አውጅ ፤ ዕዳዬ ይሰረዛል ጭንቀቴም ይበናል ብለህ አውጅ ። ብቻ ከአፍህ አሉታዊ ሳይሆን አዎንታዊ አዋጅ ይውጣ ። ዕድልህ የተመሠረተው ከአፍህ በሚወጣው አዎንታዊ አዋጅ ላይ ነው ። ሁለተኛው “ የመስጠት ሕግ ” ( the law of giving / tithing ) ነው ። አንዳንዶች ይህን አራዝመው “ ከመዝራት ሕግ ” ጋር ያዛምዱታል ። ገንዘብ እንደ ዘር ነው ፤ እናም ገንዘብ የሚዘሩ ገንዘብ ያጭዳሉ (“ seed money ”)። የሚሰጡ ያለ ምንም ጥርጥር ይሰጣቸዋል ፤ የሚበትኑ ይሰበስባሉ ። ባጭሩ የድህነት እርግማን በመስጠትና በመዝራት ሕግ ይቀለበሳል ።
መቼም ከሀብትና ከብልጽግና ጋር ምንም ጠብ የለኝም ። ብልጽግና ወይም ገንዘብ በራሱ እኩይ አይደለም ፤ ሀብት ወይም ንዋይ በራሱ ክፉ አይደለም ። ይሁንና “ ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ” እንደ ሆነ ፣ ገንዘብ የሰዎችን ሁለንተና ለመቈጣጠርና ሰዎችን ከእግዚአብሔር መንገድ ለመንጠቅ ብርቱ ጉልበት እንዳለው መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያስተምራል ( 1ጢሞ 6 ፥ 10 ፤ ሉቃ 16 ፥ 13 ፤ ማር 10 ፥ 17-31 )። ገንዘብን ከምንም በላይ መውደድ ከዐሠርቱ ትእዛዛት መካከል
የመጀመሪያውን ትእዛዝ ይተላለፋል ( ዘጸ 20 ፥ 1-2 )። ጳውሎስ በመልእክቱ ባለጠጋ ለመሆን የሚፈልጉ ሰዎችን በብርቱ ገሥጿል ። ባለጠጋ ለመሆን የሚፈልጉ ሰዎች በጥፋት ማለትም በሚጎዳ ምኞትና በፈተና ወጥመድ ይወድቃሉ ። እንዲያውም አንዳንዶች ባለ ጠግነትን ሲመኙ “ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወግተዋል ” ( 1ጢሞ 6 ፥ 11 ) ይላል ። ባለጠጋ ለመሆን መመኘትና መጓጓት “ ኑሮዬ ይበቃኛል ” ( 1ጢሞ 6 ፥ 6 ) የሚለውን አዲስ ኪዳናዊ እሴት ከመጻረሩም በላይ በሁለቱ መካከል መሠረታዊ ልዩነት እንዳለ ይገልጻል ፤ የክርስቶስ ወገን የሆኑ ሁሉ የትኛውን እሴት መከተል እንዳለባቸው መምረጥ ይኖርባቸዋል ። ጳውሎስ እግዚአብሔርን መምሰል “ ኑሮዬ ይበቃኛል ” ከሚለው ጋር ሲያነጻጽር ባለጠጋ ለመሆን መፈለግን “ ራስን በብዙ ሥቃይ ከመውጋት ” ጋር አነጻጽሮታል ። ባለጠጋ ለመሆን መፈለግ ራስን ለፈተና ወጥመድ ምቹ አድርጎ ማቅረብ ነው ። “ ኑሮዬ ይበቃኛል ” ማለት “ እጅግ ማትረፊያ ነው ”። መላው አዲስ ኪዳን ባለን ነገር ረክተን እንድንኖር ያስተምራል ። አዲስ ኪዳን ትልቅ ትርፍ ወይም እሴት ነው የሚለው ባለን ነገር ረክቶ መኖርን ነው ። ይህንን ነው ጳውሎስ “ እውነተኛ