Christian Books & Magazines - Free Berea Magazine 5 | Page 30
የአካል ብልቱ
የአካል ብልቱ አለመስማማቱ
ቀርቶ አንድነቱ ቤተሰብነቱ
አንዱ ያለ አንዱ ላይቆም ሙሉ ሆኖ
አንዱ አካል ከሌላው ሲኖር ተጨካክኖ
አንድኛው ካንደኛው አንድ ላይ ተጣብቆ
አካል ላይለያይ ሀሳብ ተራርቆ
እራስ ያለ አንገት ሁሉን ላይቃኝ ዞሮ
መስራት ላይቻለው ያይንን ስራ ጆሮ
አሽቶ ላይለየው አፍ እንደ አፍንጫ
እፍንጫም እንደ አፍ ላይሆን ጣእም መስጫ
ደካማ መሳዩ የአካሉ ክፍል
ስንኩል ሊያረግ ሁሉን ታናሹ ቢጎድል
ከዚያ ካንዱ መንፈስ ከውሃው ጠጥቶ
አንዱን መንግስት ሊወርስ እዚህ ተገፋፍቶ
ብቻውን ሊወጣ ሌላውን አጣጥሎ
የሱን ፀጋ ሊያገን የወንድሙን ገድሎ
ያንዱ አካል ብልቶች ምነው ተለያዩ
ደርሰው እንደ ጠላት እንደዚህ ተያዩ
የእግዚአብሔር ቤተሰብ ....
ባላገር አድርጎት እንዳይሆን እንግዳ
የገዛ ወንድሙን ሲያየው እንደባዳ
አይ ብልት ሞኙ ሰው
አንደኛው ያላንዱ ያየውን ላይወርሰው
ሁሉን ለኔ ለኔ ለኔ ብቻ ብሎ
ከገዛ ወገኑ ልቡን አስኮብልሎ።
አፍንጫን ሲመቱት ላይቀር አይን ማልቀሱ
ካንድ ዘር ተወልዶ አይ ሆድ መባባሱ
ብቻውን ቢቀመጥ አካል ተገንጥሎ
ከመጣል ላያመልጥ ከወገኑ ጎድሎ
ካንደኛው ቢነጠል በሌላው ታጅቦ
ጌታውን ላያመልክ አንድ እጅ አጨብጭቦ
መለየትን ወዶ መሆን ሲሻ ሌጣ
ተግባሩን ለብቻው ችሎ ላይወጣ
መብራት ብርጭቆውን ወግድልኝ ቢለው
ነፋስ መጥቶ ወዲያው እንደሚያጨልመው
30
ሁሉን ድንቅ አድርጎ ፈጣሪ አስውቦ
መልክ ቢለያይም ባንድነት ሰብስቦ
ብልቶችን ሁሉ አድርጎ ያንዱ አካል
አንዱን ላንዱ ሰጥቶ ምንም እንዳይጎድል
መስማት ብቻ ቢሆን አይን ሁሉ ታውሮ
ጆሮ እያዳመጠ መውደቅ ተደናብሮ
ባንዱ ያለውን ስራ ሌላው ላያሟላ
እየተገፋፋ ብልት ሲጠላላ።
በዚያ በሸለቆ አጥንት ደርቆ ደርቆ
አንዱ አጥንት ካንዱ አጥንት እጅግ ተራርቆ
ተስፋ ታጥቶባቸው በህይወት የማይኖሩ
ዳግመኛ ተነስተው ነፍስን የማይዘሩ
በእግዚአብሔር ቃል ትንቢትን ተናግሮ
በመንፈሱ እስትንፋስ በህይወት አኑሮ
አጥንትን ሲያለብስ ጅማትና ስጋ
ትንፋሽን ሲሰጠው ቁርበት ሲዘረጋ
በሰው ልጅ ተነግሮ ለንፋስ ትንቢቱ
በህይወት እንዲኖሩ የተገደሉቱ
መንፈሱ ሲመጣ ሲወርድ በላያቸው
ታላቅም ሰራዊት አድርጎ አቆማቸው
የተለያዩትን አጥንቶች ሰብስቦ
አንድ ያረገው መንፈስ ሁሉን አቀራርቦ
በእውነት በጸጋው በቃሉ አድሶ
የጥልን ግድግዳ ዳግም አፈራርሶ
አካል ጤና እንዲሆን ምንም ማይጎድለው
ፈጣሪ ብልትን ራርቶ እንዲፈውሰው
እየተዋደደ ሁሉ ተከባብሮ
የአምላኩን ትእዛዝ ይፈፅም ተፋቅሮ
ምስጋና እንዲበዛ ላምላካችን ክብር
መቀራረብ እንጂ መለያየት ይቅር ።
ከእህት ሃና ከበደ (ኢያኤል)