Christian Books & Magazines - Free Berea Magazine 5 | Page 3

በወንድም ሚካኤል ዓለሙ
አሜን !

ርዕሰ-አንቀጽ

የጥማት መሬት የውኃ ምንጭ ትሆናለች

ኢሳይያስ 35 ፥ 7

በወንድም ሚካኤል ዓለሙ

ነቢዩ ኢሳይያስ ይሄንን ትንቢት ሲናገር ፥ ሁለት ምልከታዎች ነበሩት ። አንደኛው ለ70 ዓመታት ያህል በባቢሎን ምርኮ በባርነት የነበረው ሕዝብ ወደ አገሩ ወደ ጽዮን ለመመለስ እድል ሲያገኝ ፥ አገሩ ከመድረሱ በፊት ያለውን ምድረ በዳና ደረቅ መሬት እያሰበ ፥ ወደ ተስፋይቱ ምድር የምገባው እንዴት ይሆን ? አውሬውንስ እንዴት አድርጌ ነው የማልፈው ? ያን የጥማት መሬት … ደረቁን መሬት ..... ምድረ በዳውን እንዴት እሻገረዋለሁ ? እያለ ሲጨነቅ በመንፈሱ የተረዳው ነቢይ ፥ እግዚአብሔር በደረቅ ምድረ በዳና በጥማት መሬት የውኃ ምንጭ እንደሚያፈልቅና ፥ ሕዝቡም እግዚአብሔር ያፈለቀውን የውኃ ምንጭ እየተጎነጨ በደስታና በዝማሬ ፅዮን እንደሚገባ ነው ።
ሁለተኛው የነቢዩ ኢሳይያስ ምልከታ ፥ በእውነተኛ መንፈሳዊ ጥማት ለሚቃጠሉና ለሚጠሙ ሕዝቦች ሁሉ የመሲሁ የአዳኙ የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ መምጣት እውን እንደሚሆን ፥ የምድረ በዳውን ጉዞም በእርሱ የህይወት ውኃ ምንጭነት አጠናቀው ጽዮን እንደሚገቡ አሻግሮ የተመለከተበት ነው :: ይህ ከእግዚአብሔር አፍ የወጣ ቃል ዛሬም የሚሰራና ሁሌም ህያው ነው :: ካለንበት መንፈሳዊ ድርቀትና ጥማት የምንወጣው የህይወት ምንጭ በሆነው በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ ነው ።
ከአበሻ ምድር በተለያየ ምክንያት ወጥተን ፤ በሰሜን አሜሪካ ፥ በካናዳና በአውሮፓ ተበትነን የምንኖረውን እኛን ፤ እግዚአብሔር አሰበን ። የቤርያ መስመር ሰው ባላሰበውና ባላቀደው ፥ ነገር ግን ድንቅ በሆነው በእግዚአብሔር አሰራር ከ7 ዓመታት በፊት ተጀመረ :: በዚህ አገልግሎት ብዙ ነፍሳት ወደጌታ ሲጨመሩ ፥ የደከሙና ወደኋላ የቀሩ ሲመለሱ ፥ በህመም የነበሩ ሲፈወሱ በአጠቃላይ በርካታዎች ሲጽናኑ ምስክሮች ሆነናል :: ክብር ለእግዚአብሔር ለአምላካችን ይሁንና ሁላችንም የዚህ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ነን ። በመንፈሳዊ ድርቀት የተመታ ሁሉ የህይወት ምንጭ የሆነውን ኢየሱስን እየተጎነጨ የጽዮንን መንገድ ተያይዞታል ። ክብር ለጌታ ለኢየሱስ ይሁን ።
የቤርያ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አገልግሎት ሰባቱንም ቀን 24ቱንም ሰዓት በስልክ መስመሩ ላይ አገልግሎቱን ይሰጣል ። እንዲሁም በኢትዮጵያና በኤርትራ የወንጌልን ስራ እየሰራ ነው ። ይሄ የወንጌል አገልግሎት የተጀመረው የዛሬ 5 ዓመት የመጀመሪያውን ኮንፍራንሳችንን ዴንቨር ኮሎራዶ ላይ ስናደርግ ቅዱሳን የሰጡትን ገንዘብ እንደ ምርት ዘር በመጠቀምና 10 ወንጌላዊያንን በማሰማራት ነበር ። ኢትዮጵያ ውስጥ የወንጌልን ሰራ በመስራት ላይ ከሚገኘው ከታላቁ ተልእኮ ጋር በመተባበር 10 የወንጌል ሰባኪዎችን በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በማሰማራት የተጀመረው ይሄ የወንጌል አገልግሎት ባሁኑ ጊዜ ያሉት አገልጋዮች ወደ 150 ደርሰዋል ። በዚህም አገልግሎት በብዙ ሺህ ለሚቆጠሩ ወንጌል የተመሰክሮላቸው ሲሆን ጌታን የተቀበሉት ደግሞ ክትትል እየተደረገላቸው ነው ። አስደናቂ ምስክርነት ያላቸው ብዙዎች ወደ ጌታ የመጡ ሲሆን 45 ጅምር ቤተክርስትያኖችም ተተክለዋል ።
እቅዳችን የወንጌል አገልጋዮችን በመጨመር ወንጌልን ለፍጥረት ሁሉ ማዳረስ ነው ። ግባችን ደግሞ ፍጥረት ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ድኖ ማየት ነው ። በጥማት መሬት የውኃ ምንጩን እየጠጣን እስከ ጽዮን እንድንደርስ ጌታ ይርዳን :: ለሆነውም ሆነ ለሚሆነው ሁሉ ክብር ለጌታ ለኢየሱስ ክርስቶስ ይሁን ።

አሜን !

3