Christian Books & Magazines - Free Berea Magazine 5 | Page 23

ባለቤት እንደሆነ ተረዳ ። የአደባባይ ሰው ሆኖ ፣ በየማዕዘኑ ላይ በሌሎች ፊት ለመታየትና የዝናን ተራራ ለመቆናጠጥ ሲል ስለ ወጣው ከንቱ ዳገት ተጸጸተ ። የድሮው አሳዬ በአዲስ መረዳት ብቅ አለ ፣ ለዛ ደብዝዞ ለነበረው ሕልሙ ማስፈጸሚያው እውነት በራለትና ጉልበት አገኘ ። በጸሎት እየጠየቀ ፣ ጌታን እየታዘዘ አብሮ ሊወጣ ቃል ገብቶ ሲነሳ : “ የአደባባይ ሰው ሆነህ ፣ በየማዕዘኑ ላይ ቆመህ ፣ ሰውን አይተህ በሰው ታይተህ “
የሚለው የተስፋዬ ጋቢሶ መዝሙር ወደ አንደበቱ መጣ ።
ያ በሄደበት የቤተሰብ ስብሰባና ለቅሶ ቤት ሁሉ ቃል ሳያካፍል ለአለመውጣት ሲታገል የነበረው አሳዬ ዛሬ ሌላ ሰው ሆኖ ጥግ ይዞ “ ከራስ በላይ ነፋስ ” የሚል ይመስላል ። ድሮ የሚያውቁት ፣ አሳዬ ክርስትናውን ትቷል ሲሉ ፤ አንዳንዶች ደግሞ “ እሱ ድሮም ክርስትና አልገባውም ነበር ” በማለት ይተቹታል ። በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን አሳዬ ከሃይማኖተኛነት ወደ ክርስትያንነት መለወጡን የሚረዱ በጣም ጥቂቶች ናቸው ።
በሚሄድበት ስፍራ ሁሉ በአብዛኛው የሚቀመጠው ጌታን ከማያውቁ ሰዎች ጋር ነው ። በተገኘበት ስብሰባ ተነስቶ ከመጸለይ ይልቅ ስለ
ስብሰባው አስቀድሞ በቤቱ ጸልዮ ይመጣል ። “ እግዚአብሔር ዘወትር በስራ ላይ ነው ” ብሎ በማመን መንፈስ ቅዱስ ሲሰራ አብሮ ለመስራት ራሱን አዘጋጅቶ ከቤቱ ይወጣል ። የራሱን አዳራሽ ለመሙላት ሰው የመሰብሰብ ተልዕኮም የለውም ። በተጠራበት ሁሉ ሰዎችን ለመርዳት ፈጣን ነው ። ስለ ኑሮ ፣ ስለ ትዳር ፣ ስለ ልጆች ፣ ስለ ትምህርት ፣ ስለ መንግስት ፣ በአጠቃላይ ሰዎች ሁሉ ስለሚያልፉበት የዚህ ዓለም ችግር በቅንነት ያዳምጣል ። ሲናገርም በሃይማኖታዊ አስመሳይነት ያልተከሸነ ጥበብ የተሞላ ምላሽ ይሰጣል ። ከብዙዎች ተዋውቆ ስልክ ቁጥራቸውን ይቀበላል ። ከሁለት ወይም ሶስት ሰዎች ጋር ደግሞ በሳምንቱ ውስጥ አብሮ ቡና ለመጠጣት ቀጠሮ ተለዋውጦ ወደ ቤቱ ይሄዳል ።
አሳዬ ጸሎቱም ተቀይሯል ። የድሮው በይገልበጥ ተጀምሮ በይደፋ የሚያልቀው ጸሎቱ ተለውጦ በአብዛኛው በመማለድና በመቃተት የሚጸልየው በሳምንቱ ውስጥ ስለተዋወቃቸው ጌታን የማያውቁ ሰዎች ነው ። በድምጽ ማጉያ ፣ በፍላየር ፣ በማስቸገር እና በክርክር ሳይሆን ፤ ጌታ ሰዎችን ወደ ራሱ እንደሚጠራና የእርሱ ድርሻ ጌታ ሲሰራ አብሮ ለመስራት መታዘዝ እንደሆነ ሚስጥሩ ገብቶታል ። የዛሬው አሳዬ ሰዎችን በመልካም ግንኙነት በመቅረብ መመስከር ( Relational Testimony ) የአገልግሎት ሸክሙ
መንፈሳዊ መጽሔት

ለማንበብ tsega . com

ነው ። በዚህም ሰዎችን ለጌታ በመማረክ የተሳካለት አገልጋይ ሆኗል ።
ዛሬ እነዚያን የፍንዳታ ዘመናት ሲያስብና ለምስክርነት ይጠቀምባቸው የነበሩትን የማስፈራሪያ ቃላት ፣ ያለቦታው የሚጠቅሳቸውን ጥቅሶችና በጀብደኝነት የተሞሉ ጠላትን ሳይሆን ጎረቤት አዋኪ ረብሻ-መሰል ጸሎቶች ሲያስብ ይገረማል ። የአደባባይ ሰው የመሆን ናፍቆት ያናወዘውና በግብዝነት የተንከራተተበት ዘመን ዛሬም ይታወሰዋል ።
ከ ዚ ህ ከአሳዬ ታሪክ ብዙ እንደምንማር አምናለሁ ። በጌታ እግር ስር ቁጭ ብለው ሳይማሩ ፣ ክብርና ዝናን በመመኘት ወደ አገልግሎት የሚሮጡ ሁሉ ተመሳሳይ ጥፋት በራሳቸው እና በሌሎች ላይ እንደሚያደርሱ የታወቀ ነው ።
በርግጥ ሁላችንም ጌታን እንደተቀበልን የመጀመሪያው ናፍቆታችን ያልዳኑ ዘመዶቻችንና ጓደኞቻችን እኛ ያገኘነውን እንዲያገኙ ሲሆን ፤ ለዚህም በየዋህነትና በቅንነት ለሁሉ መንገር ፣ ከሁሉ ጋር መከራከርና የፍርድና የማስጠንቀቂያ መዓት ማውረድ የተለመደ ነው ። በዚህም ብዙዎችን በማስቆጣትና እልህ እንዲገቡ
23