Christian Books & Magazines - Free Berea Magazine 5 | Page 11

ከወንድም ዶ / ር ተስፋዬ ሮበሌ

አግድም አደጉ የእምነት እንቅስቃሴ አስተምህሮ

በሰባዎቹ መጨረሻ ጀምሮ የኮሪያዊው ሰባኪ የፖል ዮንጊ ቾ 1 ስብከቶች በካሴት ተዘጋጅተው በአገሪቱ ውስጥ በስፋት ይሠራጩና ይደመጡ እንደ ነበር አስታውሳለሁ ። በተለይ ፣ “ ዘ ፎርዝ ዳይሜንሽን ” (“ The Fourth Dimension , Vol . 1 and Vol . 2 ”) 2 በሚል ርእስ የታተሙት ሁለት ቅጽ መጻሕፍት ፣ ብዙዎች እጹብ ድንቅ በማለት አሞካሽተውት ነበር 3 ። ከሊቅ እስከ ደቂቅ በትምህርቱ ያልተደመመ ፣ ከአምላክ ማደሪያ / ጸባኦት በቀጥታ የተቀዳ መገለጥ መሆኑን ያላጸደቀ ግለሰብ ያለ አይመስለኝም 4 ። የዐቅብተ እምነት አገልግሎት ብቻ ሳይሆን ፣ ነገረ መለኮትም በቅጡ በማይታወቅበት በዚያ ጨለማ ዘመን ፣ አለማወቅን ተገን አድርጎ የተነሣው ይህ ትምህርት ፣ አላንዳች ከልካይ እንደ ተዛማጅ በሽታ አገሪቱ ላይ ናኝቶአል ፤ የቤተ ክርስቲያንንም አስተምህሮና ሥነ ምግባር ክፉኛ በርዟል ።
ከመነሻው የብዙዎችን ልብ የሳበው ይህ ትምህርት ፣ ከሱ በኋላ ለመጡት መሰል “ የእምነት እንቅስቃሴ ” ትምህርቶች 5 ትልቅ የማደላደል ሥራ ሠርቷል ። የእንቅስቃሴው ልሳን የነበረውና በእንግሊዝኛ ቋንቋ ታትሞ በአገሪቱ ውስጥ በስፋት ይሠራጭ የነበረው “ አክትስ ” መጽሔት ፣ ለእንቅስቃሴው ማበብ ትልቅ ድርሻ ነበረው ። ኋላ በእንቅስቃሴው አስተምህሮ የደቆኑ የናይጄሪያ ሰባኪያን ወደ አገሪቱ በስፋት በመግባት ፣ በጽሑፍና በካሴት የተሠራጨውን መከር በጥቂት ወራት መሰብሰብ ችለዋል ፡፡ ምናልባት ትምህርቱ ሞተ ሲባል ዐፈር እየላሰ የሚነሣው ፣ ከተገመተው በላይ ሥር ስለሰደደ ይሆንን ? እኔ በዚህ ጽሑፍ ይህ እንቅስቃሴ እምነትን አስመልክቶ የሚያስተምረውን ትምህርት እተቻለሁ ።
1 ኋላ ፣ “ አምላክ ስሜን እንድቀይር አዞኛል ” ካለበት ጊዜ ጀምሮ ፣ ዴቪድ ተብሎ ይጠራል ፡፡ ታክስ በማጭበርበር እንዲሁም የቤተ ክርቲያኒቱን ገንዘብ ሃያ ሚሊዮን ዶላር ለራሱ ጥቅም በማዋል በተደጋጋሚ ክስ ቀርቦበታል ፡፡ እንደ ጐርጐሮሳውያኑ የዘመን አቈጣጠር የካቲት 20 ቀን 2015 ዓ . ም ታክስ በማጭበርበር ወንጀል ተከሶ ለሦስት ዓመት ዘብጥያ ተወርውሯል ፡፡ ከእስራት ቅጣቱም በተጨማሪ አምስት ሚሊዮን ዶላር መቀጫ እንዲከፍል ተበይኖበታል ፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የበኲር ልጁ ከአባቱ ጋር አባሪ ተባባሪ በመሆኑ ምክንያት የሦስት ዓመት የእስር ቅጣት ተጥሎበታል ፡፡ የተለያዩ ምንጮች ግለሰቡ ባካሄደው ወንጀል መጸጸቱን ዘግበዋል ፡፡ የዚህን መረጃ እውነተኛነት ፣ “ ዘኢኮኖሚስት ”፣ “ ክርስቲያኒቲ ቱደይ ” እንዲሁም “ ጎስፕል ሄራልድ ” ላይ ማረጋገጥ ይቻላል ፡ ፡ ምንጮቹ እነሆ :— The Economist 15 October 2011 ፡ http :// www . gospelherald . com / articles / 50492 / 20140224 / david-yonggi-choreflects-on-guilty-verdict-hardest-day-of-50-years-of-ministry . htm # ixzz3NKvvPnz4 http :// www . christianitytoday . com / gleanings / 2014 / february / founder-of-worlds-largest-megachurch-convicted-cho-yoido . html
2 David Yonggi Cho ( 1979 ), The Fourth Dimension ( Vol . 1 ): Discovering A New World of Answered Prayer , ( Bridge-Logos , Alachua , FL , USA ). David Yonggi Cho ( 1983 ), The Fourth Dimension ( Vol . 2 ): More Secrets for a Successful Faith Life ( Bridge-Logos , Alachua , FL , USA ). 3 እኔ በበኩሌ ኑፋቄ እየኰመኰምን ማደጋችንን ያስተዋልሁት ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ከገባሁ በኋላ ነው ፡፡ 4 እኔ እስከማውቀው ድረስ ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ትምህርቱ ስሕተት እንደ ሆነ በተደራጀ መንገድ ይፋ ያደረጉት ፣ የቤዛ ባፕቲስቶቹ ለዐከ ታፈሰና ፍሥሓ ደጀኔ ናቸው ። ኋላ ግን በርካታ ሰዎች ትምህርቱ ስሕተት ነው ሲሉ ሞግተዋል ፤ ለምሳሌ የሙሉ ወንጌሉ ወንድም ተሾመ ነጋሽ ፣ የመካነ ኢየሱሱ ዶ / ር ሽመልስ አድማሴ ፣ የቃለ ሕይወቱ ግርማዊ ቡሽ ፡፡ ኋላ ማለትም በሰማንያዎቹ መጀመሪያ ላይ ፣ የአብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ባዘጋጀው ዐውደ ጥናት ላይ ፣ እኔን ጨምሮ የመሠረተ ክርስቶሶቹ ወንድም ሰሎሞን ከበደና ወንድም ሰሎሞን ጥላሁን እንዲሁም ዶ / ር ሽመልስ አድማሴ በትምህርቱ ስሑትነት ላይ ሒስ ሰንዝረናል ፡፡
5 ምንም እንኳ ቾ ትምህርቱን በቀጥታ ያገኘው ፣ አምላክ በጸሎት ጊዜው እየመጣ ከሚናገረው ንግግር እንደ ሆነ ቢገልጽም ፣ ከእነዚህ በርካታ መገለጦች በኋላም ፣ ለተባለው ነገር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ እንዳገኘ ቢያስረዳም ፣ ማኮኔል የተባለው አሜሪካዊ ጸሓፊ ፣ ዲቪድ ዮንጊ ቾ ይህን ትምህርት በቀጥታ የቀዳው ከእምነት እንቅስቃሴ መምህራን ማለትም ከኢ ደብሊው ኬኒየንና ከኬኔት ሐጌን እንደ ሆነ በማስረጃ ሞግቷል ፡፡ D . R . McConnell ( 1988 , 1995 , 2007 ), A Different Gospel ( Updated Edition ): A Bold and Revealing Look at the Biblical and Historical Basis of the Word of Faith Movement .
11