AddisLidet 2017 - Page 8

መዝራትና ማጨድ

መዝራትና ማጨድ

በዶ / ር አዳም ቱሉ
“ በምድር ዘመን ሁሉ መዝራትና ማጨድ …… አይቁዋረጡም ” ዘፍጥረት 8 ፣ 22
ትናንትና ያለፍንባቸው ከፍታና ዝቅታዎች በዛሬው ኑሮአችን ላይ ጥለውት የሚያልፉት መልካም ትዝታ ወይም ክፉ ጠባሳ አለ ፡፡ ሁላችንም ዛሬ የምንኖረው ይሄንኑ የትናንት ትዝታና ጠባሳ ከሁዋላና ከፊታችን እያብለጨለጭን ነው ፡፡ ጠባሳው የጎላና የተለቀ ሲሆን ሌሎች ራሳቸውን የሚያዩበት መስታወት ሆኖ ” እኔን ያየህ ተቀጣ ” ወይም “ የኔን ፈለግ ተከተል ” እያለ ባደባባይ ይጮሀል ፡፡ ስለመዝራትና ማጨድ ሲነሳ መታወቅ ያለበት ሰዎች የሚከተሉትን አራት አይነት ዘሮች በሕይወታቸው ሊያጭዱ እንደሚችሉ ነው ፡፡ ሰው ራሱ የዘራውን ያጭዳል ፣ ሌላ ሰው የዘራውን ያጭዳል ፣ ወፎች የዘሩትን ያጭዳል ፣ ወይም መሬቱ ላይ የነበረውን ( ድጋሚ የበቀለውን ) ያጭዳል ፡፡ ከነዚህ አራቱ አጨዳዎች መሐል ሰው ሁሉ ራሱ የዘራውን ማጨዱ ባይቀርለትም ሌሎቹን ሶስቱን እንዲያጭድ ግን በጨረታው አይገደድም ፡፡ ገላትያ 6 ፣ 7 ሲናገር “ አትሳቱ እግዚአብሔር አይዘበትበትም ሰው የሚዘራውን ሑሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና ” እንደሚል የጊዜ ርዝመትና እጥረት ካልሆነ በቀር የዘራነው መብቀሉና የዘራነውን ማጨዳችን አይቀርም ፡፡ በየቤተክርስቲያኑ ያለው አንዱ የዘመናችን ተግዳሮት ሰዎች ያልዘሩትን “ መልካም ” ነገር ለማጨድ መስክ ወጥተው መንፈሳዊ ጠኔ ጥሎአቸው የተፈጠረ የረሐብተኝነት ቀውስ ነው ፡፡ አንዳንዶቹ ባቄላ ዘርተው ጤፍ ለማጨድ ስለሚሞክሩ ባዶ ከረጢት ይዘው በየአደባባዩ ይንከላወሳሉ ፡፡ ከነዚህ የባሰው ደግሞ ምንም ሳይዘሩ ለማጨድ የሚነሱ ህልመኞች ሲሆኑ
እነዚህ ውሐ የሌለባቸው ደመናዎች እግዚአብሄርን የመፈለጋቸው ምክንያት በሰማይ ያለችውን የእርሱን ፈቃድ ለመፈጸም ሳይሆን በምድር ያለችውን የነርሱን ፈቃድ ለማስፈጸም ነው ፡፡
ይህ የሕልም ኑሮ የምድራችንን ክርስትና አንገት እየጠመዘዘ ዛሬ ዛሬ ክርስትና ዋጋ የሚያስከፍልና ጠባብ የጽድቅ መንገድ መሆኑ ቀርቶ ሁሉን የሚያማልል ፣ አሪፍ የሚያስብል ፣ አራዳ የሚያስብል ፣ ዘመናዊ የሚያስብል ፣ ሐብታም የሚያስብል እየሆነ መጥቶአል ፡፡ የምንደኞችን ከርስ ለመሙላት በሚተጋ ትውልድ መሐል ትምህርቱና ስብከቱ ፣ ኮንፍረንሱና መነቃቃቱ ሁሉ እግዚአብሄርን እየመሰሉ ለመኖር የሚያስችለንን ትጥቅ ለማግኘት ሳይሆን በአቋራጭ መንገድ የልባችንን መሻት ለማስፈጸም ኢላማ ያደረገ ቢሆንም ዛሬም ሰዎች እያጨዱ ያሉት የዘሩትን ነው ፡፡ አንዳንዶች ዛሬ “ የተሳካላቸው ” ቢመስሉንም ገና ዘርተው ስላልጨረሱ ታግሰን አጨዳቸውን መጠበቁ ብልሕነት ነው ፡፡
እውነተኛ ደቀ መዝሙር የሚያደርገን እግዚአብሔር የልባችንን አውቆ ባደባባይ ስለገለጠው ሳይሆን እኛ የእግዚአብሕርን የልቡን ሐሳብ ይህም በክርስቶስ ኢየሱስ ራሱን ለአለም መግለጡን አውቀን ለስራው ስንመቸው ነው ፡፡ እኛ በሰማይ ያለው አባታችን አምባሳደሮችና ጉዳይ አስፈጻሚዎች ነን እንጂ እግዚአብሄር የእኛ ጉዳይ አስፈጻሚ አይደለም ፡፡ ክርስትናችን መሰረት ጌታ የልባችንን እንዲነግረንና “ እንዲባርከን ” ብቻ ከሆነ የልባችንን ሐሳብ የሚተነብዩልንን ተንባዮች ስናሳድድ ዘመናችንንና ገንዘባችንን እንዳንጨርስ ጌታ በሰጠን ለም መሬት ላይ ዘራችንን በትጋት ዘርተን መልካሙን አዝመራ የምናዘምርበት ዘመን መጥቶአል ፡፡
ይቅጥላል ...
8