AddisLidet 2017 | Page 4

የአዲስ ልደት ቤተክርስቲያን የእምነት አቋም
1 . እግዚአብሔር
እግዚአብሔር አብ ዘለዓለማዊ ፣ የማይወሰን ፣ ፍጹም ፣ ራሱን በመንፈስ ቅዱስ በሚገልጥና ሁሉን በሚችል በሁሉ ቦታ በሚገኝ ሁሉን በሚያውቅ በማይለዋወጥ ፣ የሚታየውንና የማይታየውን ሁሉ በፈጠረ በእግዚአብሔር አብ እናምናለን ፡፡ ዘፍጥረት 1 ፡ 1-31 ; ዘፍጥረት 2 ፡ 7 ; 1ቆሮንቶስ 8 ፡ 6 ; 2ቆሮንቶስ 6 ፡ 18 ; 1ጢሞቴዎስ 1 ፡ 17
1.2 ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር አብ ልጅ መሆኑን ፣ በመንፈስ ቅዱስ ከድንግል ማርያም መወለዱን ፣ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው መሆኑን ፣ ስለ ኃጢያታችን በመስቀል ላይ የተሰቃየና የሞተ የተቀበረ በሶስተኛውም ቀን ከሞት በአካል ተነስቶ ለሰዎች ተገልጦ በክብር ወደ ሰማይ ያረገ መሆኑን ፣ አሁንም በአባቱ ቀኝ ተቀምጦ ዘወትር ለእኛ እንደሚማልድልን ፣ ዳግመኛም በታላቅ ክብርና ሥልጣን እንደሚመለስ እናምላለን ፡፡ ማቴዎስ 16 ፡ 16 ፣ የሐዋሪያት ሥራ 5 ፡ 30-31 ፣ ማቴዎስ 1 ፡ 23 ፣ 1ቆሮንቶስ 15 ፡ 3-8 ፣ የሐዋሪያት ሥራ 1 ፡ 9-11
1.3 መንፈስ ቅዱስ ፍፁም አምላክ ፣ አጽናኝ ፣ አስተማሪና ወደ እውነት የሚመራ መንፈሳዊ አባቶችን ፣ ነቢያትን ፣ ሐዋርያትን ያንቀሳቀሰና የመራ ፣ በአማኞችም ውስጥ አድሮ መንፈሳዊ ስጦታዎችና ኃይልን በማከፋፈል ቤተክርስቲያንን እንደሚያንጽ ፣ ዓለምንም ስለኃጢአት ፣ ስለጽድቅና ስለፍርድ እንደሚወቅስ እናምናለን ፡፡ የሐዋርያት ሥራ 2 ፡ 1-11 ; 2ጴጥሮስ 1 ፡ 21 ; የሐዋሪያት ሥራ 1 ፡ 8 ; 1ቆሮንቶስ 12 ፡ 4-11 ; ኤፌሶን 4 ፡ 11-12 አማኞች በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እንደሚጠመቁ እናምናለን ፡፡ ማርቆስ 16 ፡ 17-18 ; የሐዋርያት ሥራ 10 ፡ 44-46 በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 2 መሠረት ዛሬም አማኞች በመንፈስ ቅዱስ ተሞልተው በልሳን መናገርን ፤ በፀሎትና በእምነት ሊቀበሉት እንደሚገባ ከክርስቶስ የተሰጠ ትዕዛዝ መሆኑን እናምናለን ፡፡ የሐዋርያት ሥራ 1 ፡ 4-5 ፣ 2 ፡ 1-4 ፣ 2 ፡ 38-39 ፣ ኤፌሶን 5 ፡ 18 በሐዋርያት ዘመን እንደነበረ በዘመናችንም የመንፈስ ቅዱስ የፀጋ ስጦታዎች ለአማኞች እንደሚሰጥ እናምናለን ፡፡ 1ቆሮንቶስ 12 ፡ 1-11 ፣ በዚህም ዘመን በቤተክርስቲያን ኢየሱስ ክርስቶስን በማክበር በአማኞች ውስጥ ሆኖ እንደሚሠራ እናምናለን ፡፡ ዮሐንስ 16 ፡ 7-15
1.4 ስላሴ በአካልና በስራ ሶስት በመለኮታዊ ባህሪና አምላክነቱ አንድ አምላክ መሆኑን እናምናለን ።
2 . አዲስ ፍጥረት ( ድነት ) ሰው በመጀመሪያ ያለ ኃጢአት መፈጠሩን እናምናለን ፡፡ ይሁን እንጂ አዳም በፈቃደኝነት ኃጢአት ላይ በመውደቁ ምክንያት ሰው ሁሉ የኃጢአት ባህሪ ይዞ መወለዱን እናምናለን :: ነገር ግን ስለ ሀጢያቱ ተጸጽቶና ንስሐ ገብቶ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ ግል አዳኙና ጌታው አድርጎ የተቀበለ ሰው ሁሉ ፤ ከመንፈስ ቅዱስና ከእግዚአብሔር ቃል የተወለደ አዲስ ፍጥረትና የእግዚአብሔር ልጅም መሆኑን እናምናለን ፡፡ ዘፍጥረት 1 ፡ 26-28 ፣ ዘፍጥረት 3 ፡ 1-24 ፣ ሮሜ 10 ፡ 9-10 ፣ ዮሐንስ 1 ፡ 12-13
4