AddisLidet 2017 | Page 28

ከዓመታት በኋላ አንድ ወዳጄን በስልክ አገኘዋት እጅግም ደስ አለኝ ። እንዳገባችም አጫወተችኝ ቀጠል እርጋም መፀነስዋን ስትነግረኝ ልጎበኛት ወደ ቤትዋ አቀናሁ ። እውነት ለመናገር ደስታዬ ወደር አልነበረውም ። መኖሪያ ቤትዋ እንደ ደረሰስኩ ድንቡሽ ቡሽ ብላ አገኘዋት ። “ ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ ።” እንደሚል ቃሉ ከደስታዬ ብዛት ጉንጮቼ በእንባ እራሱ ።
ጥቂት ከተጫወትን በሁዋላ አልበም እንዳይ ጋበዘችኝ ። ፎቶዎቻቸው እጅግ በጣም ያምራሉ ! ነገር ግን በቤተክርስቲያን ከነበረው ስርዓት ውጪ የሚዜዎች ሆነ የተጋባዥች ፎቶ ባለማየቴ ሌላ አልበም ትሰጠኝ ይሆናል ብዬ ስጠብቅ ሳለሁ “ ይኸውልሽ የእኔ ሰርግ ብድር የለውም ዋናው በእግዚያብሔር እና በሰው ፊት ቃል ኪዳን መግባት አይደል ።” ብላ ዓይን ዓይኔን ታየኝ ጀመር ። ንግግርዋን ቀጠለች እንዲህ ስትል “ ከአስር የማይበልጥ ሰው መናፈሻ ሄደን በአገልግል የተያዘ ምግብ በልተን ፎቶ ተነስተን ፕሮግራሙን አጠናቀቅን ወደ ቤታችን ተመለስን ። እንደው እውነት እንነጋገር ከተባለ ዋናው ማስታወሻው አይደል ።” ስትለኝ ደንገጥ አልኩና ዝም ብዬ ፎቶዎቹን ሳይ ከምትነግረኝ ነገር ጋር አልጣጣም አለኝ ። ምክንያቱም የቬሎዋ ፣ የቶክሲዶው ፣ የፎቶዎቹ ፣ የመናፈሻው ማማር ትልቅ ሰርግ አስመስሎታልና ።
መደንገጤ ገባትና “ ስሚኝማ በብድር ትልቅ ሠርግ ደግሰን ነገ እኔና ባሌ ፍቅርን ከማጣጣም ይልቅ ዕዳን እያሰብን ከምንጨነቅ ይሄ አይሻልም ?” ስትለኝ እውነት ነው ብዬ አንገቴን በመነቅነቅ መልስ ሰጠዋት ። ቀጠለች …. “ አንድ ወዳጄ ምን አለኝ መሰለሽ ከአቅም በላይ በብድር የሚሰረግ ሰርግ ማለት ሙሽሮች ለጊዜው በትልቅ ማማ ላይ ተቀምጠው ቁልቁል እያዩ ነገ የሚወርዱበትን ገደል የማየት ያክል ነው አለኝ ። እኔም ቁልቁል ያለውን ገደል አሰቤ ሠርጌን አቀለልኩት ።” ንግግርዋ እውነት ያዘለ እና የብዙዎች ችግር መሆኑን አያስተዋልኩ በተመስጦ ማዳመጤን ቀጠልኩ ። “ ደሞ እኮ ገንዘቡ ብቻ ሳይሆን ድካሙ እና ጭንቀቱ ለበሽታ ይዳርጋል ። ይኸውልሽ ዛሬ ተበድሬ ሠርግ ባለመደገሴ አሁን ቤት ገዝተናል በሚቀጥለው ሳምንት ወደ አዲሱ ቤት እንገባለን ።” ስትለኝ በጣም በመደነቅ አስተዋይነታቸውን አድንቄ ትዳራቸውን ከልቤ ባረኩ ።
ኑሮን እንደ ቤት እንጂ እንደ ጎረቤት ለመኖር መጣር አደጋው ብዙ ነው ። እንደ አቅማችን ለመኖር መወሰን ግን አትራፊ ያደርጋል ። ደግሞስ ቃሉ በመጠን እንድንኖር ያዘን የለ ? ለማንኛውም ሰርግ እያሰባችሁ ላላችሁ ትምህርት እንዲሆን ብዬ ነውና በድግስም ሆነ ያለ ድግስ ለምትሰርጉ ሁሉ በማስተዋል እንዲሆን እመክራለሁ ። አቅም ኖሮት በድግስ ያገባ መልካም አደረገ አቅሙን አውቆ ያለ ድግስ ያገባ ደሞ የተሻለ አደረገ ።
መልካም ጋብቻ ! ሻሎም !
በሩት ( ቹቹ )
28