AddisLidet 2017 | Page 27

እንደዚህ ቀን ሕይወት ጣፍጦኝ አያውቅም ፡፡ ወዲያውም የደህንነት ትምህርት ለመማር ወስኜ በሶስተኛው ቀን ከፓስተር አልአዛር ጋር ትምህርቴን ጀመርኩኝ ፡፡ የደህንነት ትምህርቴ አንድ ቀን ሳልቀር በየሳምንቱ ለአንድ አመት ከስምንት ወር ተምሬ በ2013 ዓ . ም የውሃ ጥምቀት መሰድኩኝ ፡፡
የአሁኑ ኑሮህ ምን ይመስላል ? ከዚህ በሁዋላ ለአመታት አጥቼው የነበረውን እውነተኛ ሰላም ለመጀመሪያ ጊዜ ስላጣጣምኩኝ መሰለኝ ዝም ብዬ ሰውን መውደድ ጀመርኩኝ ፡፡ በቤተክርስቲያን የሚዘጋጁ ፕሮገራሞችንም በትጋት እካፈላለው ፡፡ እንዲሁም በተከፈተልኝ በር ሁሉ ማገልገል ጀምሬ ባሁኑ ወቅት በቤተክርስቲያን ውስጥ በሳውንድ ሲሰተምና በጸሎት አገልግሎት ውስጥ አገለግላለው ፡፡ በኑሮዬም እኔና ቤተሰቤ በጣም ደስተኞች ነን ፡፡ ተጨማሪ ስጦታ ባለፈው አመት ጌታ አንድ ወንድ ልጅ ሰጥቶናል ፡፡ ልጆቼም በቤተክርስቲያን ውስጥ የሰንበት ትምህርት ይማራሉ ጌታ መልካም ነው ፡፡
ስለ ወደፊትስ ምን ታያለህ ፣ ምንድነው ተስፋህ ? እኔ ከሞት ያመለጥኩኝ ሰው ነኝ ፡፡ ከዚህ በሁዋላ ጌታን በምችለው ሁሉ እያገለገልኩኝ መኖር ነው የምፈልገው ፡፡ ሰዎች በተለያየ ምክንያት ሊያገለግሉ ይችላሉ እኔ ግን የማገለግለው ውለታውን እያሰብኩኝና የቤተክርስቲያንን ቀዳዳ ለመድፈን ነው ፡፡ እስካሁን ባለኝ አገልግሎቴ የሚሰጡኝን ስራዎች እንደሸክምና እዳ ሳይሆን እንደ እድል ስለምቆጥራቸው የታክሲ ስራዬን ትቼ ስመጣና ሳገለግል ምንም ቅር አይለኝም ፡፡ ወደፊትም የራሴን ስራ እየሰራሁኝና ኑሮዬን እየኖርኩኝ በሙሉ ሐይሌ ማገልገል ፍላጎቴ ነው ፡፡ ዛሬ በጌታ ቤት ብኖርም ነገ ከድካሜ በቀር ይሄ ነው የምለው የራሴ የሆነ ብርታት ስለሌለኝ ነገ ጌታ እንደሚፈልገው አይነት ሕይወት ይኖረኝ ይሆን ? ብዬ እሰጋለው ፡፡ ስለዚህም ለኔ ትልቁ ጥማቴ ጌታ ቶሎ በመጣና የዚህን አለም ሕይወቴን በለወጠው ብዬ ነው ፡፡
አሜን ማራናታ ! ስለሰጠኸን የህይወት ምስክርነት እናመሰግናለን ጌታ ይባርክህ !
27