AddisLidet 2017 - Page 25

እናቴ ከአባቴ ከተለያየች በኃለ ጌታን ተቀብላ በአዲስ አበባ ሙሉ ወንጌል ቤተክርስቲያን ታመልክ ስለነበረና ከእኔም ጋር አልፎ አልፎ እንገኛኝ ስለነበር ለታመመችው ልጅ ጸሎት ቢደረግላት መፍትሔ እንደሚሆናት ነገረችን ፡፡ አኔና ባለቤቴም ይህንን ጸሎት ለመሞከር እናቴ ወዳመራችን አዲስ አበባ ሙሉ ወንጌል ቤተክርስትያን ልጄንና ባለቤቴን በ1996 ላኩዋቸው ፡፡ ልጄ ተጸልዮላት ሕመሙም ተሽሎአት ብትመጣም ከሁሉ በላይ በቤታችን ለውጥ የሆነው ግን ባለቤቴ ለልጄ ለማስጸለይ ወደ አዲስ አበባ በሔደች ጊዜ ጌታን ተቀብላ መምጣትዋ ነበር ፡፡ በባለቤቴ ጌታን መቀበል ምክንያት በቤታችን አዲስ ነገር መሆን በጀመረበትና ኤማ ከተወለደች ከሶስት አመት በሁዋላ ሁለተኛ ልጃችንን ኢቱን ጌታ ሰጠን ፡፡
የባለቤትህ ጌታን መቀበል አንተን አላስቆጣህም ? የእርስዋ ጌታን መቀበል አላስቆጣኝም ፡፡ እንደውም ደስ ነው ያለኝ ፡፡ የሚገርመው በዛን በብዙ ሀጢያትና ሱስ በተሳሰረ ሕይወት ውስጥ እየኖርኩኝ ጌታ ትክክለኛ መንገድ እንደሆነ ይሰማኝ ነበር ፡፡ አንድ የማስታውሰው ነገር ፣ በዛን ጊዜ የወንድማችንን የዳኔኤል አምደሚካኤልን ‹‹ ሞኝነት ሆኖ አይደለም ›› የሚለውን መዝሙር በካሴት ቀድቼ በሔድኩበት መጠጥ ቤት ሁሉ እያስከፈትኩኝ እሰማ ነበር ፡፡ ምንም የሚገባኝ ነገር ባይኖርም አንዳንዴ ክርስትና ትክክለኛ እምነት እንደሆነ ከሰዎች ጋር እከራከር ነበር ፡፡
ባለቤትህ ጌታን ካገኘች ቡኃላ ምን ለውጥ መጣ ? ባለቤቴ ጌታን ካገኘች ቡኃላ ሕይወትዋ ሙሉ ለሙሉ ተለወጠ ፡፡ በብዙ የጥፋት ስራዎቼ ተባባሪ የነበረችው ባለቤቴ በቀጥታ ክፋቶቼን ባትቃወማቸውም እንደቀድሞው መተባበርዋን አቆመች ፡፡ ከሁሉ በላይ ለኔ ጥፋቶች የተሻለ ቀና አማራጭ ትሰጠኝ ነበር ፡፡ በዚህ ወቅት የእርስዋ ጌታን መቀበልና ለኔ የተሸሉ አማራጮችን ማቅረብ ከብዙ ጥፋቶችና ወንጀሎች ከልክሎኛል ፡፡ ከሁሉ በላይ በ2000 ዓ . ም ወላጅ አባቴ በሞት ሲለየን በኔና በቤተሰቤ ሕይወት ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣ ነገር ተፈጠረ ። አባቴ ከአራት ሚስቶች የሚወለዱ 13 ወንድምና እህቶች
ስለነበሩት አባቴ በሞተበት ወቅት ውርስ ለመከፋፈል በተነሳ አለመግባባት ከአንዳንድ ወንድሞቼ ጋር ከፍተኛ ጠብ ተፈጠረ ፡፡ አባቴ ከገንዘብና ጥቃቅን ንብረቶች ተጨማሪ ወደ 8 ከባድ መኪናዎች ፣ በቃሊቲ ከተማ አንድ መጋዘንና አንድ የለስላሳ ማከፋፈያና ትልቅ የመኖሪያ ቤት ስለነበረው በወንድማማቾች መሐከል የነበረው ጥል ለመገዳደል እስከመፈላለግ ደርሶ ነበር ፡፡ እኔም በዚሁ ምክንያት አንዱን ወንድሜን ተጣልቼ ስለነበር እርሱን ለመግደል ሽጉጥ እስከማዘጋጀት ደርሼ አጋጣሚዎችን ስጠብቅ ባለሁበት ሰአት ባለቤቴ እኔን ለማትረፍ ስትል ዲ . ቪ ቪዛ ሞልተን ከተሳካ ወደ አሜሪካ እንድንመጣ ትወተውተኝ ጀመር ፡፡ የሰናይት ፍላጎት አሜሪካ መምጣት ሳይሆን እኔ ከገባሁበት ክፉ አላማ ለማስቀየር ነበር ፡፡ ሰናይት የሞላችው ዲ . ቪ ሲመጣ እኔ ከሀገር ለመውጣት ፈቃደኛ ስላልሆነኩኝ ሎተሪው ተቃጠለ ፡፡ በቀጣዩ አመት በድጋሚ የሞላችው ዲ . ቪ ሎተሬ ወጣልንና በፌብሩዋሪ 21 2009 ዓ . ም . ተጣድፈን ወደ አሜሪካ መጣን ፡፡ በሕልሜም በውኔም አስቤው የማላውቀው አሜሪካ ሀገር ቤተሰቤን ይዤ አዲስ ኑሮ ጀመርን ፡፡
የአሜሪካ ኑሮአችሁን እንዴት አገኘከው ? አሜሪካ ገብተን ከወንድሞቼ ጋር የነበረኝ መጋደልና አስቤው የነበረው ደም መቃባት ቢቀርም የኔ ሕይወት ግን አሁንም ስላላረፈ ነፍሴ አሁንም ትባዝናለች ፡፡ ወደ አሜሪካ ስንመጣ የተቀበሉን ቤተሰቦች የሚችሉትን ሁሉ አድርገው እንደ አቅማቸው ራሳችንን እስከምንችል አስተናገዱን ፡፡ አኔም በመጣሁ በሁለት ወሬ ሾፐርስ ውስጥ በየሜዳው የተበተኑ የገበያ ጋሪዎችን ( ካርቶችን ) መሰብሰብ ስራ አግኝቼ ብቀጠርም ባለፉት ዘመናት ከሞተር ብስክሌት ላይ ወድቄ እግሬን ተሰብሬ ስለነበረ እያመመኝ መጣ ፡፡ ሐኪም ቤት ሔጄ ስመረመር ከዚህ በሁዋላ ከባድ ስራ ቆሞ መስራት እንደሌለብኝ ስላስጠነቀቁኝ ስራዬን አቆምኩኝ ፡፡ ከዚህ በኃላ ለኔ የሚሆን ስራ ማግኘት ከባድ ፈተና ሆነብኝ ፡፡
25