AddisLidet 2017 | Page 22

የእግዚአብሔር ጉብኝት ዝግጅትን ስለሚጠይቅ የእግዚአብሔር ዓላማ እና ሀሳብ እንደገና እንዲገለጥ ልንጸልይ ፣ ልንጾም ፣ ልናምጥና ልንማልድ ብሎም በፅድቅ እና በቅድስና ልንኖር ይገባናል ፡፡ የእግዚአብሔር ዓላማ ሙሽራዋን ያካተተ እና የያዘ ስለሆነ ጊዜውን ተረድቶ ራሱን በሰጠው ሰው አላማውን ይፈጽማል ፡፡ የእግዚአብሔር ዓላማ ይከናወን ዘንድ ለስራው የተዘጋጀ ሰው ለመሆን የምንመርጠውና የምንወስነው እኛው ነን ፡፡ የእግዚአብሔርን የጉብኝት ዘመን ያስተዋሉ ቅሬታዎች በዘመናት መሐል ራሳቸውንና ቤተክርስቲያንን ለከበረው ሙሽርነት ራስዋን እንድትቀድስ ምክንያት ሆነዋል ። እግዚአብሔር ባዘጋጀው የክብር ዙፋን ላይ ከበጉ ጋር ሊቀመጥ የሚያስብ የበሰለ እና ያደገ አማኝ በዚህ ምድር ቆይታ በፈተና ጸንቶ ጠርቶና ነጥሮ ሊወጣ ግድ ነው ፡፡ ቤተክርስቲያን ከሁለት ሺህ ዓመት በላይ ታሪኳን ስታከብር የከረመችው የመዳንን አስፈላጊነት በመስበክ ላይ መሆኑ ትክክል ቢሆንም መዳንን እንደመጨረሻ ግብ አድርጎ መውሰድ ግን ስህተት ነው ፡፡ ምክንያቱም ደህንነት ወደ እግዚአብሔር ዋና ዓላማ መንገድ መቆናጠጫ እንጂ በራሱ ፍጻሜ አይደለም ፡፡ እግዚአብሔር ልጁን እየሱስን የላከበት ዋና ዓላማ እንድንድን ብቻ ሳይሆን በኑሮና በሕይወት የልጁን መልክ እንድንመስልም ነው ፡፡ ስለ ዳንን ብቻ ሁሉን ያገኘን እና የተከናወነልን እየመሰለን ወደ ውስጥ ከመግባት እና ከመዝለቅ ይልቅ በባህር ዳር ተቀምጠን አሸዋ እንድንሰፍር እግዚአብሔር አይፈልግም ፡፡ የበጉ ሀሳብ መዋጀት ብቻ ሳይሆን በዳንኤል 9 ፡ 23 እና በብዙ የወንጌል ክፍሎች እንደምናየው እግዚአብሔር የሚጠራን ወደዚያ ስፋቱ ፣ ርዝመቱ ፣ ከፍታውም ፣ ጥልቀቱም ምን ያህል መሆኑን ለማስተዋል ከመታወቅም የሚያልፈውን የእርሱን ፍቅር ለማወቅ እንበረታ ብሎም እስከ እርሱ ፍፁም ሙላት ድረስ ደርሰን እንሞላ ዘንድ ነው ፡፡ ይህ
ደግሞ በመዳናችን ከተቀበልነው ፍቅር ያለፈ ፣ የበረታ እና የጠለቀ ስለሆነ ራስን ማዘጋጀት ይጠይቃል ። ይህ አይነቱ ፍቅር ወደ እግዚአብሔር ልብ በጥልቀት የሚያስገባ ፍቅር ከመሆኑም በላይ ሌሎችን የምንሸከምበት ሰፊ ትከሻ ይሰጠል ። ሰው ከዳነ በኋላ በመንፈሳዊ ጉዞው ላይ ሙሽራውን በጉጉት እንደምትጠብቅ ሙሽራ ራሱን አዘጋጅቶና ከነውር ሁሉ ጸድቶ ቢጠብቅ በፊቱ ላለው ጉዞ ስንቅ ይሆንለታል ፡፡ መጨረሻም ፣ በእግዚአብሔር ዕቅድና ሀሳብ ውስጥ ከመዳን ያለፈ እሳቤ ስላለ ተግተን የጉብኝታችንን ጊዜ እናፋጥን ፡፡ ጌታ በሕብረት ፣ ለቤተክርስቲያንና በግል ለእያንዳንዳችን የጉብኝት ዘመን ስላለው ከእጮኝነት ለሙሽርነት ወደሚያበቃን መንፈሳዊ መታደስ እና እድገት ልንጓዝ ያስፈልጋል ። የእግዚያብሔር ጉብኝት ሲመጣ እንዳያልፈን ፀጋው ይርዳን ።
ሻሎም !
ሩት ( ቹቹ )
22