AddisLidet 2017 | Page 21

እጮኛ ወይስ ሙሽራ . . . ?

እጮኛ ወይስ ሙሽራ . . . ?

በሩት ( ቹቹ )
በቅድሚያ እየኖርንበት ያለው ዘመን ምን አይነት እንደሆነ ጠንቅቆ ማወቅ ብሎም እግዚአብሔር በዚህ ባለንበት ዘመን ሊያደርግ ያለውን ነገር ምንድነው ብሎ መጠየቅ እግዚአብሔር ሊያከናውን ባለው ሀሳብ እና እቅድ መካተት ያስችለናል ፡፡ የእግዚአብሔርን የጊዜውን ሀሳብ ለመረዳት የዳንኤልን መጽሐፍ ጅማሬ መመልከት መልካም ነው ፡፡ ምክንያቱም አሁን የምንኖርበት ዘመን በዚያ ዘመን ከተኖረው ኑሮ ጋር እጅግ ተመሳሳይነት አለው ። በመጀመሪያው እግዚአብሔር ከዘላለም የሞት ፍርድ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል አድኖን በመስቀሉ ፍቅርን ፣ ፍርድን ፣ እውነትንና ጥበብን ስለገለጸልን እጅግ አድርገን ልናመሰግን ይገባል ፡፡ አማኝ በህይወት ሳለ ሙሽራ በመሆን ስፋቱ እና እርዝመቱ ከፍታውም ጥልቀቱም ምን ያህል እንደሆነ ከመታወቅም የሚያልፈውን የክርስቶስን ፍቅር በማወቅ ይበረታ ዘንድ እስከ እግዚአብሔርም ፍፁም ሙላት ደርሶ ይሞላ ዘንድ የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ዓላማ እና ሀሳብ ነው ፡፡ ለዚህ ደግሞ የአማኙ ፈቃድ እና አዎንታዊ ምላሽ ያስፈልጋል ፡፡ ዓለም ሳይፈጠር ለመረጠን እና ወደ እርሱ በፍቅር ለጋበዘን ምላሻችን እጃችንን ከልባችን ጋር አንስተን አዎን ይሁንልን እንድንል ይጠበቅብናል ፡፡
ቤተክርስትያን እግዚያብሔር ወዳየላት እንድትመለስ በስሙ የተጠራ ህዝብም የዚህ ስም ታላቅነት እና ገናናነት በትክክል ገብቶት መንቀሳቀስ ይገባዋል ፡፡ እግዚአብሔር የእኔ የሚላቸው እና የሚወራረድባቸው ሰዎችን በዚህ ዘመን ሲያገኝ የእኔ ናችሁ እኔም የእናንተ ነኝ ይላቸዋል ፡፡ በትንቢተ ዳንኤል 9 ፡ 2ዐ ላይ ዳንኤል የኢየሩሳሌም መፍረስ የሚፈጸምበትን
ሰባውን ዓመት ፥ እግዚአብሔር በቃሉ ለነቢዩ ለኤርምያስ የተናገረውን የዓመቱን ቍጥር በመጽሐፍ ያስተውላል ፡፡ ስለዚህም ራሱንና በምርኮ ባቢሎን የነበሩትን ሕዝቡን በአምላኩ ፊት ይዞ ሲቀርብ እናየዋለን ፡፡ በዳንኤል ዘመን የነበረው የእግዚአብሔር ክብር በህዝቡ መካከል መጥፋትና የእግዚአብሔር ሕዝብ ግራ የተጋባ ኑሮ አሁን በምድር ላይ ላለችው ቤተክርስቲያም የሚሠራ ይመስለኛል ፡፡ በዘመናችን የእግዚአብሔር ምስክርነት በቤተክርስቲያን የጠፋ የሆነበት ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር የሚወራረድባቸው እና የእኔ የሚላቸው ሰዎች በመታጣታቸው ነው ፡፡ በዳንኤል ዘመን ለራሳችን ስም እና ክብር እንስጥ የምትለው ባቢሎን በዚህ ዘመንም በቤተክርስቲያን ስሯን ሰዳ ተመሳሳይ ጥፋት እያመጣች ነው ፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔር ጥሪ ራዕይ 17 እና 18 እንደሚነግረን “ ክርስቲያኖች ሆይ ንቁ ከባቢሎን ውጡ ” የሚል ነው ፡፡ ጌታ ከመምጣቱ በፊት ከባቢሎን ወጥተው ባቢሎንም ከውስጣቸው የወጣ ለራሳቸው ስም እና ክብር መስጠት የማይሆንላቸው ወንድ እና ሴት የእግዚአብሔር ልጆች ሊገለጡ የግድ ነው ፡፡ መፅሐፍትን ስንመረምር ራሷን ያዘጋጀች ሙሽራ የክርስቶስን መምጣት ታፋጥናለች ፡፡ ራዕይ 19 እንደሚነግረን " የበጉ ሰርግ ስለደረሰ ሚስትም ራስዋን ስላዘጋጀች ደስ ይበለን ሃሴትም እናድርግ ፡፡ ክብርንም ለእርሱ እናቅርብ ፡፡" ይላል ፡፡ ዳንኤል ያለበት ጊዜ ምንነት እንደገባው እኛም የጌታ የጉብኝት ጊዜ እንደደረሰ ልንገነዘብና ለጉብኝቱ ልንዘጋጅ ይገባናል ፡፡
ይቅጥላል ...
21