AddisLidet 2017 | Page 20

'' ኢየሱስም ሰዎቹ እንዲቀመጡ አድርጉ አለ ፤ በዚያም ስፍራ ብዙ ሳር ነበረበት ፡፡ ወንዶችም ተቀመጡ ቁጥራቸውም አምስት ሺህ የሚያህል ነበር ፡፡ ኢየሱስም እንጀራውን ያዘ ፡ አመስግኖም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ ፤ ደቀ መዛሙርቱም ለተቀመጡት ሰዎች ሰጡዋቸው ፡፡ '' ቁ . 11-12 :: ከላይ እንዳነበብነው እጃቸው ላይ ያለውን ያውም የራሳቸው ያልሆነ ግን በመካከላቸው የተገኘ የአንድ ብላቴና እራት ጌታ ተጠቀመበት ፡፡ አመስግኖ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ ፡፡ በአዕምሮአቸው ምግቡ መሀል ቢያልቅስ ?፣ ባይዳረስስ ? ወዘተ ... የሚሉ አሳቦች ይኖራሉ ፡፡ ነገር ግን እነርሱን እንተዋቸው ፡፡ ዝም ብለን ባለን ነገር እንጀምር ፡፡ አርሱ አያሳፍረንም ፡፡ በጣም መጠንቀቅ ያለብን መነሻ ላይ ማነው የተናገረኝ ? የሚለው ላይ ብቻ ነው ፡፡ ራዕዩ የትኛውንም ያህል ትልቅ ይሁን እግዚአብሔር ተናግሮን ከሆነ መፈጸሙ አይቀርም ፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ለህዝቡ ቆርሰው ማደል ጀመሩ ፤ አይናቸው እያየ ሁሉ እንደሚፈልገው መጠን ወስዶ ፣ ጠግቦ ፣ የተረፈውን ቁርስራሽ 12 መሶብ ሞሉ ፡፡ የኛ ጌታ እንደዚህ ነው ! የመጨረሻውን ውጤት ከመነሻህ ጋር ማመሳከር እስኪያዳግት ድረስ የሚባርክ አምላክ ነው ፡፡ ጌታ በጣም ትልልቅ ነገር የሰራባቸውን ሰዎች ምስክርነት መመልከት እንችላለን ፡፡ ለምሳሌ ዎርልድ ቪዥን ዛሬ ላይ በብዙ ሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ካፒታል ከመድረሱ በፊት መነሻ ካፒታሉ ቦብ ፒየርስ የሚባል የድርጅቱ መስራች በወንጌል ምክንያት የተሰደደችን አንዲት ብላቴና በጊዜው ከረዳበት አምስት / 5 / የአሜሪካን ዶላር እንደተጀመረ ጋሽ በቀለ ወልደኪዳን ስለ ዎርልድ ቪዥን በጻፈበት መጽሐፉ ላይ ታሪኩን አስፍረውታል ፡፡ ከብዙዎች ንግግር እንደተረዳሁት ሁሉም ክርስቲያኖች ማለት ይቻላል በተለይ ከሆነ ጊዜ በሁዋላ በህይወታቸው አንዳች ነገር ሰርቶ የማለፍ ጥማት ውስጥ ይገባሉ ፡፡ ግን ከየት ? እና እንዴት ? እንደሚጀምሩት አያውቁም ፡፡ ለምሳሌ ብዙ ህጻናትን የማሳደግ እና አዛውንቶችን የመንከባከብ አልያም ሌሎች በጎ የልማት ስራዎችን ስለ
መስራት አስበው ከሆነ ቢያንስ ከአንድ ህጻን ወይም አንድ አዛውንትን ከመርዳት መጀመር ሊኖርባቸው ይችላል ፡፡ ከቆይታ በሁዋላ ስራው / ራዕዩ / እየሰፋ ይሄድና ለብዙዎች ጥላ ለመሆን ይበቃል ፡፡ ራዕዩ ከጌታ ይሰጠን እንጂ ያለንን ጥቂት ነገር ባርኮ መጀመር ብቻ ነው ፡፡ ጥርት ያለ ራዕይ ተቀብለው ለመጀመር ሚሊዮን ብሮችን ሲጠብቁ ፣ ራዕያቸው አጀንዳቸው ላይ ብቻ የቀረባቸው አያሌዎች ናቸው ፡፡ የምንፈልጋቸው ውጤቶች ስንጠብቃቸው ሳይሆን እየሰራን እያለ የሚመጡ ነገሮች ናቸው ፡፡ ከመጠበቅ መንፈስ ወጥተን ባለን ነገር እንቅስቃሴ ውስጥ እንግባ ፡፡ ነገሮች እንደ መብረቅ ድንገት ላይከሰቱ ይችላሉ ፡፡ ትልልቅ ነገሮችን እጃችን ባለው ትንሽ ነገር እንጀምራቸው ፡፡ ነገ ትልቅ የማይሆኑበት ምክንያት የለም ፡፡ አንዳንዶቻችን ይህ እውቀት ጎድሎን ነው ነገራችንን ያዘገየነው ፤ አንዳንዴም ያበላሸነው ፡፡ እስኪ ዛሬ እንደገና ለመነሳት እንሞክር ፤ ዓላማችንን አንስተን በእምነት እንጀምር ፡ መክሊታችንን ሳንነግድበት ጌታ ድንገት እንዳይመጣብን እፈራለሁ ፡፡ ነገ ዛሬ ሳንል ስንፍና መጥቶ እንደ ወንበዴ ሳይከበን ፣ ምክንያቶቻችንን ሁሉ ጥለን ፡ ራዕያችንን ለመፈጸም እንነሳ ፡፡ ቢያንስ እኮ አንድ ለወንጌል ልቡ የሚቃጠልበትን የገጠር ወንጌላዊ መርዳት ፣ አንድ ወይም ሁለት ልጆችን አስተምሮ ለቁም ነገር ለማብቃት መነሳት ፣ ወይም በተለያየ ጊዜ ከቡና ቤት በወንጌል አምነው የወጡትን ሌላ ስራ እስኪይዙ ድረስ ኑሮአቸውን ማገዝ ፣ ወይም አንድን ድሀ ቤተሰብ ፈልጎ መርዳት ፣ ወይም ትራክቶችን ማሳተም .... ወዘተ ማድረግ ይቻላል ፡፡ እንዲህ ያሉ በጣም ብዙ ብዙ በጎ ራዕዮች አሉ ፡፡ ሳንሰበሰብ በፊት ራዕያችንን እንድንፈጽመው ጌታ በቀሪ ዘመናችን በነገር ሁሉ ይርዳን ፡፡ አሜን !
ቢንያም በፍቃዱ አቦዬ / መጋቢ /
20