AddisLidet 2017 | Page 15

ቢዚ - ቢዚ ፤ ለሁሉ ጊዜ አለው ወይስ አለን ?

ቢዚ - ቢዚ ፤ ለሁሉ ጊዜ አለው ወይስ አለን ?

በወንድም ንጉሴ ቡልቻ
ጓዙን ጠቅልሎ ወደ ውጪ አገር የሚሄድ ጓደኛውን ለመሸኘት ከተሰበሰቡት መካከል የሽኝት ፕሮግራሙን ማጠቃለያ ጸሎት የሚጸልየው ሰው እንዲህ ብሎ ጸልዮአል አሉ ፡፡ “ ጌታ ሆይ ይህ ወንድማችን በሚሄድበት አገር ቢዚ ከሚባል ጋኔን እንድትጠብቀው እንለምንሃለሁ ፡፡” “ ቢዚ ” የሚባል ጋኔን መኖር አለመኖሩን መመራመራችንን ትተን ባተሌነት “ ቢዚነት ” የውጪ አገር አበሳ መሆኑ ቀርቶ ውስጥ አገርም የሚያስጨንቀን ጉዳይ እንደ ሆነ እንቀበል ፡፡ በቀጠሮ ብዛት ፣ በእንቅስቃሴ ብዛት ፣ በጉዳይ ብዛት ፣ በሥራ ብዛት ፣ በሥራ ውጣ ውረድ ፣ በማኅበራዊ ግንኙነት ብዛት ፣ በሽቅብ ቁልቁል ብዛት ፣ የአካላችን አውታር እስኪነዝሩ ተወጣጥረናል ፤ ነፍሳችን ብን ትን እስክትል እንማስናለን ፡፡ ትንፋሽ አጥሮን ስናለከልክ የሚያየን የሌላ ዓለም ፍጡር ቢኖር “ ምን ሥራሥር በጥብጠው ቢጠጡ ነው እንዲህ የሚያዛብታቸው ፣ የሚያሽከረክራቸው ” ብሎ በጠየቀ ፡፡ ለመሆኑ ምን እንዲህ ያባትለናል ? የየዕለቱ ውጣ ውረድ ነዋ ! የጉረሮ መድፈን ጥሪ ፣ የማኅበረ ሰብ ቦታችንን የማስጠበቅ ጥሪ ፣ የነገ ምን ይሆናል ጭንቀት ፣ ሌሎችም ይህን የመሳሰሉ ሁሉ ፡፡ የሰው ልጅ የሚሠራውንና የሚውልበትን ሁነኛ ጉዳይ አግኝቶ በሥራ መጠመዱ በረከት እንጂ ርግማን
አይደለም ፡፡ ጊዜ እንደ ጅረት በሚንፎለፎልበት ልማዱ ቢነጉድ የሥራ ቦይ እየቀደዱ ጥቅም ላይ የሚያውሉት የታደሉ ናቸው “ ዘመኑን ዋጁ በሚለው ምክር አብነት ፡፡ እንዲህ የሚያደርጉ በሥራው ከሚገኘው ጥቃሞት በላይ ስብእናቸው ይለማል ፣ ርካታና ደስታም ያገኛሉ ፡፡ አሁን ያነሣነው “ ጋኔኑ ቢዚነት ” ግን ከሚያለማው የሚያጠፋው የበለጠ ፣ ከሚያረካው የሚያቅበዘብዘው የበዛ ፣ ደስታችንን ቦጥቡጦ የሚበላ መልቲ ነው ፡፡ ሮጠን ሮጠን ልባችን ሊፈነዳ ሲል ስንቆም የትም እንዳልደረስን ስንረዳ ፣ ከበሬታ ፍለጋ ብዙ የአንቱታ ካባ ደርበን ድንገት ካባው የወደቀ ቀን የነፍሳችን ክሳት ሲጋለጥ የዚህ ዐይነት ቢዚነት ፍሬ ይታወቅ ይሆናል ፡፡ ወደኋላ መለስ ብለን ስንመለከት ፣ ያልተጠናቀቁ ሥራዎች ፣ ምላሽ ያልተሰጣቸው ደብዳቤዎች ፣ ያልተጎበኙ ወዳጆች ያልተጻፉ መጣጥፎችና ያልተነበቡ መጻሕፍት ይታዩናል ፡፡ በሥራ እየባተልን ቢሆንም የምናገኝበት ደስታ እያደር የመነመነ ነው ፡፡ ሆኖም ችግር የሚፈጥርብን ተግቶ መሥራት ሳይሆን ጥርጣሬና መወላወል ናቸው ፡፡ ትልቁ አደጋ ለአስቸኳዩ ጉዳይ መላ ለመፈለግ ስንጣደፍ ዋነኛውን ጉዳይ መዘንጋቱ ነው ፡፡
ችግሩ ደግሞ ዋነኛው ጉዳይ ዛሬ ወይም በዚህ ሳምንት ይሠራ የሚያሰኝ አጣዳፊነት የሌለው መሆኑ ነው ፡፡ ፈጣን ርምጃ የሚጠይቁን አጣዳፊ ጉዳዮች ናቸው ፡፡
ይቅጥላል ...
15