AddisLidet 2017 | Page 14

... ወቅት መዳረሱን ከሚያበስሩላት ወቅቶች መጨብጨብ ወይም ቅጠል ማብቀል የመጨረሻው ደረጃ ነው ። ወገኖቼ ሆይ ፍሬ ማፍራት ትልቅ ተስፋ ነው ። ተስፋው በሕይወታችን እውን እንዲሆን እነዚህን ሂደቶች በትግስትና በትጋት መወጣት አለብን ። እግዚአብሔር ወተትና ማር ወደምታፈሰው ምድር አስገባችኋለሁ ሲል ማንም በቧንቧ የሚፈስን ወተትና ማር የጠበቀ የለም ። እናንተ ንብ ማነብ ፣ ከብት ማርባት ስትጀምሩ እኔ የእጃችሁን ሥራ እባርካለሁ ማለቱ እንጂ ። ስለዚህ በሚመጣው ዘመን ስር ሰደን ለመጽናት የእግዚአብሔርን ድርሻ ለእግዚአብሔር ሰጥተን የእኛን ድርሻ በአግባቡ መወጣት ይኖርብናል ። ክርስትና የምኞትና የምትሃት ኑሮ ሳይሆን የተግባርና የመርህ ሕይወት ነው ።
መ ) ማፍራት ፦ በጊዜና በትዕግስት ሥር በመሥደድ ፣ በማበብና በመጨብጨብ ሲጠበቅ የነበረው ፍሬ አፍርቶ ማየት ሌላው ተናፋቂ ተስፋ ነው ። በጊዜው ፍሬ አፍርቶ በወቅቱ መሰብሰብ መቻል ሌላው ልዩ ትኩረትና ጥረት የሚያሻው ወቅት ነው ። ብዙ ጊዜ የተደከመበት ፍሬ ትክክለኛ ጊዜውን ባለመረዳትና በጊዜው መሰብሰብ ባለመቻል እንዳይበተን መጠንቀቅ ያስፈልጋል ። የሚጠበቀውና የመለኮት የተሃድሶ ጥሪዎች የሚያጠነጥኑት ከፍሬማነት ርቆ የወደቀውን ትውልድ ውጤታማና ፍሬማ በማድረግ ነው ። በዘር ጊዜ አልቅሰው የዘሩ በነዶ ጊዜ ደስ ብሏቸው ይመለሳሉ እንደሚል የተዘራ ሲበቅል ፣ የተጸነሰ ሲወለድ ፣ የተጀመረ ሲጨረስ ፣ የታሰበ ሲሳካ ለማየት እምነትን ሰንቆ ዘርን ለመዝራት ልንበረታታ ይገባናል ።
ሠ ) ማካፈል ፦ በመጨረሻም የእስራኤል ጥሪ ወደ አምላክዋ ፊትዋን በመመለስ በዓለም ላይ መልካም ተጽዕኖ በመፍጠር ያምላኳን ፍቅር ማካፈል እንድትችል ነበር ።
“… በፍሬያቸውም የዓለሙን ፊት ይሞላሉ ” እንደሚል ፣ የክርስትናችን ጥሪ ትባረካለህ በሚል ከፊል ነገር ላይ ብቻ የቆመ ሳይሆን ለበረከት ትሆናላችሁ በሚለዉ ለሌሎች የመትረፍ ተስፋ ቃል ላይም እንጂ ። ስለሆነም መጪው ዓመት በመልካም ነገር ለመሞላትና ለመትረፍረፍ በጃችን ላይ ያለውን ዘር የምንዘራበት ዘመን ነው ! በሚመጣው ዓመት ሕይወታችን መለኮታዊ በሆኑት መንፈሳዊም ምድራዊም በረከቶች ተሞልተን ለመትረፍረፍ የሚያበቃንን የመዝራት መርሕ አሐዱ የምንለበት ፣ በመንፈሳዊ ሕይወት የምንጠነክርበት ፣ ሊመጣ ላለው ፍሬ ስር በመስደድ ጠንክረን ራሳችንን የምናዘጋጅበት በጃችን ያለውን ዘር የምናዘምርበት ዓመት መሆኑን በአጽንኦት መግለጥና ማብሰር እወዳለሁ ። እግዚአብሔር ዘመናችንን ይባርክ !!!
መካሻው ሺመላሽ ( መጋቢ )
14